ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የማድረጉ ስራ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

115
ሰኔ 27/2011  ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የማድረጉ ስራ በሚቀጥለው  ዓመት እንደሚጠናቀቅ የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ የመንግስት የልማት ተቋማትን ወደ ግል የማዞሩ ሂደት የደረሰበትን ደረጃ  በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማደረግ ባቡር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን በከፊል  ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዞር አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ ሲዘጋጅበት የቆየው በስድስት ዘርፎች ብቻ ሲሆን እነዚህም ቴሌኮም፣ ስኳር፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ባቡር፣ ሎጂስትክስና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ ናቸው። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቴሌኮም ዘርፍ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳደግ ያላው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በትኩረት ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የቴሌኮም ስርዓት ለመዘርጋት የግሉን ዘርፍ ማበረታትም ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል። የአገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? አገራት ከገጠማቸው ችግሮች ኢትዮጵያ ምን  መማር ትችላለች? እና በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ዝግጅት እንደተደረገ ጠቅሰዋል። ''በመሆኑም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ሁለት ኩባንያዎች ብቻ እንዲሳተፉ ተወስኗል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኩባንያዎቹ በአገልግሎት ወይም በመሰረተ ልማት ዘርፍ እንደምርጫቸው ይገባም ብለዋል። ስለ ተመረጡበት መስፈርትም በሰጡት ማብራሪያ ኩባንያዎቹ የአገሪቷን ዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ዓላማን ማሳካት ይችላሉ ወይ? በመንግሥት የተያዘውን የቴሌኮም ዘርፍ ተደራሽነትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ውጥኖች ለማሳካት ዝግጁ ናቸው ወይ? የሚሉት ከግምት እንደሚገባ አስታውቀዋል። በዘርፉ "ኩባንያዎች ፍላጎት ስላሳዩ ብቻ ፍቃድ አይሰጥም" የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው የኦፕሬተሮቹ የቴክኒክ ግምገማ እንደሚካሄድም አስረድተዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የቴሎኮም ዘርፉን ወደ ግል የማዞሩ ሁኔታ እስከ ሚቀጥለው በጀት ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት ደረስ ይጠናቀቃል። የስኳር ፕሮጀክቶችንም በተመለከተ በተሰራጨው የፍላጎት መጠየቂያ ሰነድ መሰረት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቶቹን ወደ ግል ለማዞር የንብረቶች ዋጋ፣ የፋብሪካዎች አቅም ምን ያህል ነው? እንዲሁም ፋብሪካዎቹ ያላቸው አካባቢያዊ ተጽዕኖች አሉ ወይ? የሚለው እየተጠና መሆኑን አመልክተዋል። ''የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዞር ስራው በሚቀጥሉት ከስድስት ወር እስከ  አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ'' ይጠናቀቃል ሲሉም አክለዋል። በመግለጫው እንደተመለከተው የስኳር ፋብሪካዎች አዋጅ እየተዘጋጀ ሲሆን አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ስኳር የመሸጥ፣ የማምረትና፣ወደ አገር ውስጥ የሚገባና የሚወጣን ስኳር የማስተዳደር ስራን ይሰራል። በአገሪቷ ያሉ 13ቱም ኩባንያዎች ፍላጎቶች መታየቱም ተጠቅሷል።ፋብሪካዎቹ ያሉበት ይዞታ ጥናትም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም