የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አመራሮች 80 በመቶ በአዲስ ተተኩ

65
ሰኔ 28/2011 የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበረውን ማህበራዊ ሃላፊነት በተሻለ ለመወጣት እንዲያስችለው 80 በመቶ በአዳዲስ አመራሮች መተካቱን ገለፀ። ማህበሩ ከሳምንት በፊት ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ጉባኤ እስከ ወረዳ ድረስ ያለውን አመራር መለወጡን የሚገልጽ መግለጫ ዛሬ በጽህፈት ቤቱ ሰጥቷል። የማህበሩ ነባር አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በአቅም ማነስ፣ በዕድሜ ገደብ እና በመመሪያው መሠረት የአመራርነት አገልግሎት ዘመናቸው ማብቃት እንደሆነ ተገልጿል። በአዲስ ከተተኩት አመራሮች መካከል 48 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው። በየደረጃው የተዋቀረው አዲስ አመራር ማህበሩ ለወጣቱ ፍጹም እንዲወግንና የወጣቱን  ጥቅም እንዲያስከብር የሚጠበቅበት እንደሆነ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆኖ የተሾመው ወጣት ገዛኸኝ ገብረማሪያም እንደገለጸው፤ ማህበሩ ነጻ የሆነ አደረጃጀቱን በመጠቀም መንግስት የሚቀርጸውን ፕሮግራም በመከተል ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር ይፈጽማል። ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። የተመረጠው አዲሱ አመራር ማህበሩ በሚታወቅባቸው ማህበራዊ ተሳትፎ አሻራ ለማሳረፍ ለዘንድሮ ክረምት በተለያየ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን መመዝገቡን ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ተከስተ አያሌው ጠቁሟል። እንድምክትል ፕሬዚዳንቱ ማህበሩ በክረምት በጎ ፈቃድ አባላቱን ሲያሳትፍ የዘንድሮው 17ኛ ሲሆን፤ ወጣቱ ሁልጊዜ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ አካልም እንዲሆን አሳስቧል። ስለሆነም ማህበሩ ከ5ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ለሚማሩ 90 ሺህ ተማሪዎች በ114 ትምህርት ቤቶች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጡ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መዝግቧል። ማህበሩ በጎ ከሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በክፍለ ከተማ ሁለት ሁለት የአረጋውያን ቤቶችን በመለየት በጥቅሉ 20 ቤቶችን ለማደስ አቅዷል። የአዲስ አበባ ወጣቶች  ማህበር 120 ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን ደም መለገስ፣ የመንገድ ትራፊክ ደንብ ማስከበር እና ለተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል። በዚህ ክረምትም ተመሳሳይ የሆነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት መርሃ ግብር ነድፎ እየሰራ ይገኛል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም