በሉዛን በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ

320

ሰኔ 27/2011 በስዊዘርላንድ ከተማ ሉዛን ነገ በሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአሸናፊነት ተጠብቀዋል።
የ2019 ስምንተኛ ዙር ነገ 15 ሺህ 850 ተመልካች በሚያስተናግደው ኦሎምፒክ ዴ ላ ፖንታይስ ስታዲየም ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ ይካሄዳል።

በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች  ውድድር ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት እንዳገኙም የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አመለክቷል።

አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት፣ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ አትሌት ጥላሁን ሃይሌ እና አትሌት ሙክታር እድሪስ ከሚሳተፉት አትሌቶቹ መካከል በዋንኛነት ይጠቀሳሉ።

እነዚህ አምስት ትሌቶች በውድድሩ ላይ የሚያደርጉት ፉክክር በአትሌቲክስ ተመልካቹ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ5 ሺህ ሜትር እስካሁን በተካሄዱት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች 22 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አትሌት ጥላሁን ሃይሌ እና አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት በተመሳሳይ 12 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በስምንት ነጥብ ሰባተኛ፣ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አባዲ ሀዲስ በአራት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

የነገው ወድድር ተጨማሪ የዳይመንድ ሊግ ነጥብ መሰብሰብ የሚያስችል በመሆኑ ብርቱና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

አትሌት ጸጋይ ኪዳኑ፣ አትሌት ሰለሞን በሪሁ እና አትሌት ጌታነህ ሞላ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ቀሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነው እና በዳይመንድ ሊጉ 14 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አትሌት ብርሃኑ ባለው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች ውድድር በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በ1 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት አማን ወጤ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ድርቤ ወልተጂ ይሳተፋሉ።

ነገ በኦሎምፒክ ዴ ላ ፖንታይስ ስታዲየም በአትሌቲክስ እና በሜዳ ተግባራት 14 የዳይመንድ ሊግ ነጥብ የሚያሰጡ ውድድሮች\መ ይካሄዳሉ።

የ2019 ዘጠነኛው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ሞናኮ ከተማ ይካሄዳል።

በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ 14 ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራሰልስ በሚካሄደው ውድድር ይጠናቀቃል።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሬሽኖች ማህበር በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአጠቃላይ የስምንት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ በ16 የተለያዩ የውድድር አይነቶች በእያንዳንዱ ርቀት የአጠቃላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የ50 ሺህ ዶላር እና የዳይመንድ ሽልማት ያገኛል።

በተጨማሪም በእያንዳንዱ ርቀት አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከመስከረም 17 እስከ  መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለማጣሪያ የሚሳተፉ ይሆናል።

ከዚህም ባለፈ በእያንዳንዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ የ100 ሺህ ዶላር ሽልማትም ተዘጋጅቷል።