አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እና ሙዚቀኛው ሮፍናን በ'ፎርብስ' መጽሔት እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 አፍሪካውያን ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ተካተቱ

126
ሰኔ 27/2011 ኢትዮጵያዊያኑ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እና ሙዚቀኛው ሮፍናን በታዋቂው የአሜሪካ 'ፎርብስ' መጽሔት የ2019 እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 አፍሪካውያን ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ተካተዋል። የአሜሪካው ታዋቂ የቢዝነስ መጽሔት ፎርብስ በቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ እና ስፖርት ዘርፎች በ2019 በአፍሪካ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ይፋ አድርጓል። በፈጠራ ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ 30 አፍሪካውያን መካከል ለየት ባለው የሙዚቃ ቅኝት የሚታወቀው ኢትዮጵያዊው ሙዚቀኛ ሮፍናን መካተቱን የፎርብስ መጽሔት ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል። የ29 ዓመቱ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ አርቲስት ሮፍናን በአፍሪካ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 አፍሪካውያን ዝርዝር ወስጥ የገባ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ መሆኑም ተመልክቷል። የፎርብስ መጽሔት ሮፍናንን "የአዲስ አበባ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ኮከብ" በሚል የገለጸው ሲሆን በ2010 ዓ.ም ያወጣው "ነጻብራቅ" (reflection) በሚል ርዕስ ያወጣው የመጀመሪያ አልበም ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ አዲስ የሙዚቃ ድምጽ ያስተዋወቀ እንደሆነ አስታውቋል። አልበሙ ሮፍናንን በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ አድናቂዎችን ማግኘት መቻሉንና የኤሌክትሮኒክስ የሙዚቃ ስልቱ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈለት እንደሆነም ተገልጿል። በስፖርቱ ዘርፍ ከተካተቱ 30 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ የ28 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እስካሁን ኢትዮጵያውን ወክላ ባደረገቻቸው ውድድሮች 10 የወርቅ ሜዳሊያ እንዳገኘች እና አምስት የዓለም ክብረ ወሰኖች ባለቤት እንደሆነች መጽሔቱ ገልጿል። በዓለም ከሚገኙ ታዋቂ የሴት አትሌቶች በዋንኛነት የምትጠቀሰው አትሌት ገንዘቤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች በወጥ አቋም ጠንካራ ብቃቷን እያሳየች እንደምትገኝ ተመልክቷል። አትሌቷ በአትሌቲክሱ ውድድር ባሳየችው ውጤታማ ግስጋሴ እ.አ.አ በ2015 የላውሮስ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሽልማት ያገኝ ሲሆን በዛው ዓመት የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት ሽልማትን ማግኘቷን አስታውሷል። በስፖርቱ ዘርፍ ግብጻዊው የሊቨርፑል ተጫዋች መሐመድ ሳላህ፣ ሴኔጋላዊው የሊቨርፑል ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ፣ ናይጄሪያዊው የአርሰናል ተጫዋች አሌክስ ኢዎቢ በተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። በፈጠራው ዘርፍ ናይጄሪያዊያኑ ሙዚቀኞች ዊዝ ኪድ እና ቡርና ቦይ ቡርና ቦይ፣ ደቡብ አፍሪካዊ ሙዚቀኛ ሾ ማጆዚ እንደዚሁም ናይጄሪያዊቷ ዘፋኝ የሚ አላዴ ተጠቅሰዋል። የአሜሪካው ታዋቂ የቢዝነስ መጽሔት ፎርብስ በቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ እና ስፖርት ዘርፎች በአፍሪካ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 አፍሪካውያን ዝርዝር የሚያወጣው በአህጉሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ አምጪ ለሆኑ ወጣቶች እውቅና ለመስጠት ነው። የፎርብስ መጽሔት በአፍሪካ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ 30 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ የዘንድሮው ለአምስተኛ ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም