ሲዳማ ቡና ደደቢትን በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 55 አሳደገ፤ ወላይታ ድቻም አዳማ ከተማን 2 ለባዶ አሸንፏል

ሰኔ 26/2011 ዛሬ በትግራይና በወላይታ ሶዶ ስታዲየሞች በተካሄዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናና ወላይታ ድቻ አሸነፉ። በትግራይ ስታዲየም ዛሬ በተካሄደ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና ደደቢትን በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 55 ከፈ አደረገ። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አንድ ጎል በማስቆጠር መሪነቱን የያዘው ሲዳማ ቡና በ2ኛው አጋማሽ ሁለት ጎሎችን አከታትሎ በማስገባት ጨዋታውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በጨዋታው 85ኛ ደቂቃ ላይ ለሲዳማ ቡና 12 ቁጥር ለብሶ ሲጫወት የነበረው ተጫዋች ባጠፋው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳው ተሰናብቷል። የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ አቶ ዘርዓይ ሙሉ በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን መሰረት ያደረገ ጨዋታ መጨዋታቸውን ገልጸዋል። “ከዕረፍት በፊት አንድ ጎል ብቻ ብናስገባም ያገኘናቸውን እድሎች በሙሉ  አልተጠቀምንባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። በቀጣይ በሜዳቸው የሚያካሂዷቸውን ቀሪ ጨዋታዎች በማሸነፍ ለዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። የደደቢቱ አሰልጣኝ ጨዋታውን አስመልክቶ አስተያየት ከመስጠት ታቅበዋል። በተመሳሳይ ዜና ዛሬ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደው የ29ኛ ሳምንት የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የአዳማ አቻውን ያስተናገደው የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን 2 ለባዶ በሆነ ውጤት አሸነፏል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ባስቆጠራቸው ግቦች ታግዞ ነጥቡን 38 ያደረሰው የወላይታ ድቻ ቡድን በፕሪሚየር ሊግ ቆይታ ታራኩ ከፍተኛ ነጥብ መሰብሰብ ችሏል፡፡ ለወላይታ ድቻ ግቦቹን ያስቆጠሩት ቸርነት ጉግሳና ተከላካዩ ደጉ ደበበ ናቸዉ፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ባለሜዳው የወላይታ ድቻ ቡድን ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት፣ በመከላከል፣ በማጥቃትና የግብ ሙከራዎችን ደጋግሞ በማድረግ የተሻለ ሆኖ አምሽቷል። አዳማ ከተማ በመከላከልና መልሶ በማጥቃት ላይ ቢያተኩርም አጋጣሚዎችን ወደጎል መቀየር አልቻለም፡፡ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ራሱን አሻሽሎ የገባው የአዳማ ከተማ እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ የመሀል ሜዳ በመቆጣጠር፣ በማደራጀት፣ በመከላከልና ሙከራዎችን በማድረግ ጎልቶ ታይቶ ነበር፡፡ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ምንም እንኳ ወደግብ መቀየር ባይቻልም ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ የወላይታ ድቻ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ ከበደ በማሸነፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በታክቲክ የታጠረ አጨዋወት መከተላቸው እንደጠቀማቸው ገልጸዋል። ደጋፊዎችና የክለቡ አመራሮች ላደረጉላቸው ድጋፍ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ የአዳማው አሰልጣኝ አስቻለው ኃበተሚካኤል በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው በሜዳው አስቸጋሪ መሆኑን በማወቅ ነጥብ ለማስጣል አቅደው ቢገቡም በሜዳው የገጠማቸው ጭቃና ያገኟቸውን የግብ አጋጣሚዎች በአግባቡ አለመጠቀማቸው ለሽንፈት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም