ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሲጀመር አዲስ አበባ ፖሊስ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ እግኝቷል

87
ሰኔ 26 / 2011 የ2011 ዓ.ም አራተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲጀመር አዲስ አበባ ፖሊስ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። ዛሬ በተጀመረው ሻምፒዮና ወንድ 55 ሴት 14 በድምሩ 69 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የሚደረግባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጎንደር ከተማ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው። ዛሬ በውድድሩ መክፈቻ ቀን በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች የፍጻሜ ጨዋታ የአዲስ አበባ ፖሊስ ተወዳዳሪ የሆነችው ፈለቀች ሰይፉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተጋጣሚዋን ሀብታም ልዑልን በነጥብ አሸንፋለች። ውጤቱንም ተከትሎ አዲስ አበባ ፖሊስ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ በ49፣ 52፣ 60፣ 69 እና 81 ኪሎ ግራም ወንዶች የማጣሪያ ጨዋታዎች እንደተካሄዱም ተናግረዋል። የውድድሩ አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ እንደሆነም አመልክተዋል። በዚሁ መሰረት እስካሁን በድሬዳዋ፣ በወላይታ ሶዶና ደሴ ከተሞች በተካሄዱት ውድድሮች ውጤታቸውን መሰረት በማድረግ ዘጠኝ ወንድ ሁለት ሴት በድምሩ 11 ስፖርተኞችን ለመላው አፍሪካ ጨዋታ መምረጥ መቻሉን ተናግረዋል። ዛሬ በተጀመረው ውድድር ላይ የተሻሉ የሚባሉ የሴት ተወዳዳሪዎች እንደሚካተቱም ጨምረው ገልጸዋል። በአራት ዙር በሚካሄዱት ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ያሉ ውጤቶች ተደምረው በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚለይም ተናግረዋል። አራተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር እስከ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በደሴ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛ የብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን፣ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ ክለቦች አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም