ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ካይሮ ገቡ

69
ካይሮ ሰኔ 3/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለስራ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን ካይሮ ገብተዋል። የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በቆይታቸውም ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ፣ በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ። ኢትዮጵያና ግብጽ  ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በተለያዩ ጊዜያት እየተገናኙ ይመክራሉ። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ኡጋንዳን ጨምሮ በጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የስራ ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝታቸውም ከየአገሮቹ ጋር በሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የአገራቱን ትስስር የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ፈጽመዋል። ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በመጋቢት 2007 ዓ.ም ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ ግብጽን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም