የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ችግኞች ተከሉ

59
ሰመራ ሰኔ 25/ 2011 የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ በሰመራ ከተማ አካሄዱ። መርሐ ግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የችግኝ ተከላ አካል ነው። በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ድርቅና ተያያዥ ፈተናዎች ለመቋቋም ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ነባር ደኖችን መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል። በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥትና የፖለቲካ አመራሮች በተከላው ግንባር ቀደም በመሳተፍ አርአያነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። እንዲሁም የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶችም ኅብረተሰቡን ተከላውን በማስተባበር፣ በመንከባከብና እንዲጸድቁ በማድረግ የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ አቶ አወል አሳስበዋል። የክልሉ አርብቶ አደርና ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ 170ሺህ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ቢሮው 32 ወረዳዎችና በሁለት ከተሞችን አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ በተለይም ከወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችን ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ አደረጃጃቶችን የታቀፉ ወጣቶቸን በተከላው እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት አቶ አብዱ አሊ የተከሉትን ችግኝ ኃላፊነት ወስደው በመንከባከብ እንደሚያጸድቁ  ገልጸዋል። በተጨማሪም የወጣቶችን አደረጃጀት በመጠቀም ተከላው እንዲከናወን እንደሚያደርጉ በቢሮቸውም ሆነ በመኖሪያ ቦታቸው ችግኞቸን አንዲተክሉ የድርሻቸውን  እንደሚወጡ ገልጸዋል። የአፋር ክልል ባለው ቆላማ ባህርይ በአርብቶ አደርነት ኑሮውን የሚገፋ ሕዝብ መኖሪያ መሆኑ ይታወቃል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም