በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በመስኖ ግብርና የጥራጥሬና የቅባት እህል ምርትን አሳድጋለሁ...የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር

104
መቀሌ ሰኔ 2/2010 በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማብቂያ የመስኖ ግብርናን በማሳደግ የሃገሪቱን የቅባት እህልና የጥራጥሬ ምርት የውጭ ንግድ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ። አንደኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሰሊጥ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል። የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የግብርናው ዘርፍ የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ  አጋዥ ለሆኑ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ምርቶች እድገት ሚኒስቴሩ በትኩረት ይሰራል። "በተለይም የግብርና ውጤቶቹ ይበልጥ እንዲያድጉና ለሃገራችን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆኑ ለማድረግ የመስኖ ልማት ስራ በስፋት ይከናወናል" ብለዋል። ኢትዮጵያ ካላት በመስኖ ሊለማ የሚችል ወደ 11 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ መሬት ውስጥም ከአራት ሚሊዮን የሚበልጠውን በመስኖ በማልማት የግብርና ምርቷን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል። "የግብርና ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተፈላጊነታቸው እንዲያድግ ለማድረግም የምርምርና የግብይት ማዕከላትን የማጠናከር ስራ ትኩረት ይሰጠዋል'' ብለዋል ። እንዲሁም የግል ባለሃብቶችና አምራቾች፣አርሶ አደሮች፣ በቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ፣በፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት እንዲታገዙ ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፖሊስዎችና የህግ ማእቀፎች እንደሚቀረጹም ዶክተር ኢያሱ አስረድተዋል። የትግራይ ክልል የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የሰሊጥ ቢዝነስ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ተስፋይ በበኩላቸው "102 አባላት ያሉት ማህበሩ በ2009 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ ይገኛል"ብለዋል። "የሰሊጥ ምርት ከቡና ቀጥሎ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን ተናግረዋል። ማህበራቸው የሰሊጥ ምርትን ለማዘመን ከአባላቱ ውስጥ ወደ ተለያዩ ሃገራት ልኮ መልካም ተሞክሮና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉንም ገልጸዋል። ዘርፉን የሚደግፍ ፖሊሲና የህግ ማእቀፍ አለመኖር፣የብድር አቅርቦት እጦት፣እሴት የሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እጥረትና መሰል ችግሮች ከዘርፉ መገኘት የነበረበትን ገቢ እንደሚፈለገው እንዳላሳደገው ገልጸዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሀገር አቀፍ የሰሊጥ ቢዝነስ ፎረም ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የስራ ኃላፊዎች፣የምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ተመራማሪዎች፣የገንዘብ ተቋማትና በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም