የጋምቤላን የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየሰራሁ ነው — ጋህአዴን

276

ሰኔ 24/2011 የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ጋህአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኮሚቴው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የስብሰባውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለኢዜአእንደገለጹት ማዕከላዊ ኮሚቴው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሉን እየተፈታተነ ያለውን የጸጥታ ችግር መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቅርቡ በጋምቤላ ከተማና በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች  እያጋጠሙ ያሉትን የጸጥታ ችግሮች መንስኤዎች በመገምገም ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

በተለይም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶች ክልሉን ወዳልተፈለገ የጸጥታ ችግር እያስገባ ስለመሆኑ ኮሚቴው መገምገሙን ገልጸዋል።

“እንዲሁም አመራሩ ቀደም ሲል እንደነበረው ባይሆንም አሁንም ከጠባብ ብሔርተኝነትና ቡድንተኝነት አስተሳሰቦች ሙሉ ለሙሉ አለመውጣቱን ኮሚቴው ገምግሟል” ብለዋል።

በተጨማሪም በጸጥታ መዋቅር የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለም መገምገሙን ተናግረዋል።

“በመሆኑም ኮሚቴው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚሰራ አቅጣጫ አስቀምጧል”ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የጸጥታ መዋቅሮችን በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ  ኮሚቴው አቋም መያዙን አስታውቀዋል።

በአመራሩ ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እንዲፈጠር በማድረግ የክልሉን ዘላቂልማትና አንድነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ኮሚቴው ውሳኔ ማሳለፉን አቶ ኡሞድ ገልጸዋል።