ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር አመራሮች እንዲያግዙ ተጠየቀ

104
አዳማ ሰኔ 24/2011 ከብግርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር እውን እንዲሆን የሚከናወኑ ሥራዎችን  አመራሮች እንዲያግዙ ተጠየቀ። የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪን ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለስልጣን ከኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጋር በመተባበር ለወጣቶች ፌዴሬሽን አመራሮች ያዘጋጀው አገር አቀፍ የአሰልጣኞች ሥልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለጹት ወጣት አመራሮች የሀሳብና የተግባር አንድነትን በየደረጃው በመፍጠር የሕዳሴ ጎዞው እንዲሳካ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ማረጋገጥ ለዘላቂ የሥራ እድል ዋስትና በመሆኑ ይህን እውን ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ወጣት አመራሮች እንዲያግዙ ጠይቀዋል። ለእዚህም ወጣት አመራሮቹ በየአካባቢያቸው የንቅናቄ ሥራ በመስራት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን እድገት ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት። ባለስልጣኑ ለዘርፉ ልማት አጋዥ የሆኑ የአሰራርና የድጋፍ ማዕቀፎችን ከማጎልበት ባለፈ፣ አደረጃጀቶችንና አገልግሎቶችን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኢላኒ በበኩላቸው በገጠር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ በከተሞችም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በብዛት ለማፍራትና ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ወጣት አመራሮች ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር በመቀናጀትና በመደጋገፍ ራዕይ ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎችን ወደማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በስፋት ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢንዱስትሪውን በአማካይ 20 በመቶ፣ የማኑፋክቸሪን ዘርፉን 24 በመቶ በማሳደግ የአገር ውስጥ ምርትን በ2007 ዓ.ም ከነበረበት ከጠቅላላው 5 በመቶ ድርሻ በ2012 ወደ 8 በመቶ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። በ2012 በጀት ዓመት 23 ሺህ 327 አነስተኛ እና 4 ሺህ 239 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠር 562 ሺህ ዜጎች በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል። የኢህአዴግ  ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር አስፋው ተክሌ በበኩሉ በወጣቶች ንቅናቄ ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ መረጋገጡን ተናግሯል። "ይህንን እድል በመጠቀም የወጣቶችን ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ መረባረብ ይገባል" ብሏል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በእዚህ መድረክ ላይ በኢኒዱስትሪ ልማት ስትራቴጂና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባሉ መልካም አጋጣሚዎችና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ስልጠና እንደሚሰጥ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም