በዞኖቹ 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማሾ ሊለማ ነው

157
ሰኔ 24/2011 በአማራ ክልል ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማሾ ሰብል ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የየዞኑቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ። በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የመኸር ወቅት 4 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማሾ የሰብል ዘር ይሸፈናል፡፡ በማሾ ልማቱም ከ9 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ የተጠናከረ የእርሻ ሥራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። እንደ አቶ ይመር ገለጻ በመኸሩ በማሾ ከሚለማው መሬት ከ51 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል። የዘር ስራው በሐምሌ ወር መጀመሪያ እንደሚጀመር ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ የማሾን ጥቅም በመረዳቱ የማምረት ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ተሁለደሬ፣ አምባሰል፣ ቃሉ አርጎባና ወረባቦ ወረዳዎች ለማሾ ምርት ምቹ በመሆናቸው በባለሙያ ድጋፍ በትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ገለቱ በበኩለቸው በዞኑ ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማሾ ዘር ለመሸፈን የዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፡፡ “ጅሌ ጥሙጋ፣ አርጡማ ፉርሲ፣ ዳዋ ጨፋና ባቲ ዙሪያ ወረዳዎች የሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከሚለማው መሬት 90 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ አቶ ተሾመ እንዳሉት ጠቀሜታውን የተረዱ አርሶ አደሮች በበልግና በመኸር የእርሻ ወቅቶች በማሾ ምርት ላይ አተኩረው እየሰሩ ይገኛሉ። በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የባልቂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሁሴን ግጠም በበኩላቸው በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ማሾ ለመዝራት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በግብርና ባለሙያ ድጋፍና ማዳበሪያ ተጠቅመው ከሚያለሙት መሬት ከ50 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ20 ኩንታል በላይ ማሾ በማምረት አንዱን ኩንታል እስከ 2 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ በወረዳው ሞዴል ማሾ አምራች ተብለው መመረጣቸው ብርታት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ አርሶ አደር ሁሴን ገለጻ ማሾ መዝራት የመሬቱን ለምነት ከማስጠበቁም ባለፈ እንደ አርሶ አደር ሁሴን ገለጻ ነጋዴው የማሾ ምርታቸውን ማሳቸው ድረስ መጥቶ መግዛቱ የገበያ ችግር እንዳያጋጥማቸው አድርጓል። በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የወሰን ቁርቁር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ ሁሴን በበኩላቸው ሁለት ሄክታር መሬት በማልማት ከ25 ኩንታል በላይ የማሾ ምርት ለማግኘት ማሳቸውን አለስልሰው መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ማሳቸው ድረስ በመምጣት ድጋፍ ስለሚያደርጉላቸው በየዓመቱ ከምርቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ማሾ ብዙ ልፋት ሳይጠይቅ በአጭር ጊዜ የሚደርስና በገበያ ተፈላጊ መሆኑ የማምረት ፍላጎታቸውን እንዳነሳሳውም አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ወሎና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በበልግ ከለማው ማሾ ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም