በክብደት ማንሳት ሻምፒዮናው በወንዶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በሴቶች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ

173

በ15ኛው የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ሻምፒዮና በወንዶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሴቶች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሆነዋል።
ከሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጃን ሜዳ ሲካሄድ የነበረው ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በሻምፒዮናው ላይ የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሐረሪ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ  እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል።

በወንድ 40 በሴት 25 በድምሩ 65 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ከ55 እስከ 102 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ45 እስከ 71 ኪሎ ግራም ውድድሮቹ የተሳተፉባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

የአማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች በበጀት እጥረት እና በዝግጅት ማነስ በሻምፒዮናው እንዳልተሳተፉ ተገልጿል።

በ96 ኪሎ ግራም ኦሮሚያ ክልልን ወክሎ የተወዳደረው አዲሱ አለማየሁ ሻምፒዮናው ከተሳትፎ አንጻር የተሻለና ጥሩ ፉክክር እንደታየበት ገልጿል።

የሻምፒዮናው መዘጋጀት ተወዳዳሪዎች ያሉባቸውን ጉድለቶች ለመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግሯል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን የሚመራው ፌዴሬሽን የውድድር አማራጮችን ከማስፋት አኳያ እንዲሁም ስልጠናዎች ከማዘጋጀትና ክልሎች የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ከሟሟላት አንጻር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጿል።

ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንጻር ሲታይ ስፖርቱ ላይ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅና ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት እና የሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጥላሁን ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሻምፒዮናው የተዘጋጀበት አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና በሚካሄደው 12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታ የሚካፈሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው።

በዚሁ መሰረት አስፈላጊውን መስፈርት እና መለኪያ ያሟሉ በወንድ አምስት በሴት ሁለት ተወዳዳሪዎች ተመርጠው በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት ክልሎች እንዲያውቁት እንደሚደረግና ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ልምምድ እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ለክልሎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ በተመለከተ ከአንድ ወር በፊት በየክልሎቹ በመዞር ከዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን የተገኙ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደተደረገና በቀጣይ መሰል ድጋፎች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

በተለይም ከነጋዴ ይገዙ የነበሩ የስፖርት ቁሳቁሶች ውድ በመሆናቸው የግዢ ስርአቱን በመቀየር ከቻይና ለመግዛት ዝግጅት እንደተጠናቀቀም ተናግረዋል።

በስልጠና ደረጃ ፌዴሬሽኑ እስከ ኢንስትራክተርነት ደረጃ የደረሱ አሰልጣኞችን ማብቃት እንደተቻለና በየዓመቱ የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም አመልክተዋል።

አጠቃላይ ለስፖርቱ እድገት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑንና ክልሎችም ስፖርቱን ከማስፋፋትና እንዲዘወተር ከማድረግ አንጻር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሻምፒዮናው መዝጊያ በተካሄዱ አራት የፍጻሜ ውድድሮች በወንዶች 102 ኪሎ ግራም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ተወዳዳሪ ቢኒያም አክሊሉ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን ተመስገን ቶማስ ከኦሮሚያ ክልል የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

በ96 ኪሎ ግራም ወንዶች የኦሮሚያ ክልሉ አዲሱ አለማየሁ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ምህረትአብ በቀለ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃይልነት አወቀ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

ከባድ ዝናብ በመጣሉ ከትናንት ወደ ዛሬ በተላለፈው የ89 ኪሎ ግራም ወንዶች የሐረሪ ክልሉ ተወዳዳሪ ሳሙኤል በዛብህ መስፍን ሃይሉ ከኦሮሚያ ክልል እምነት ደጉ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በ71 ኪሎ ግራም ሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሏ ተወዳደሪ ምንተአምር ታደሰ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን ቤተልሄም መሳይ ከትግራይ ክልል አበባ ማዳ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በአጠቃላይ ውጤት በወንዶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በአራት ወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁለት ወርቅ እና በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ የሻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ ሆነዋል።

ድሬዳዋ ከተማ የስፖርታዊ ጨዋነት የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በሐረሪ ክልል በተካሄደው 14ኛው የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና በወንዶች የትግራይ ክልል በሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።