ኮሌጁ 907 እጩ መምህራን አስመረቀ

ጎባ ሰኔ 22/2011 የሮቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለ29ኛ ጊዜ በመደበኛውና በማታ የትምህርት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 907 እጩ መምህራን ዛሬ በዲፕሎማ አስመረቀ፡፡ ከምሩቃኑ መካከል 412ቱ ሴቶች ናቸው። የኮሌጁ ዲን አቶ ድርባ ደገፋ በወቅቱ እንደገለፁት ተመራቂዎች ለሦስት ዓመት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ተየተሰጣቸውን ስልጠና በአገባቡ ያጠናቀቁ ናቸው ። እጩ መምህራን በቋንቋ፣ በማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የሰለጠኑ መሆናቸውን ገልፀዋል ። ኮሌጁ ህጻናትን በእውቀትና በስነ ምገባር ቀርፀው ለማውጣት የሚችሉ የአንደኛ ደረጃ መምህራንን በጥራት ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ። እንደ ዲኑ ገለፃ ኮሌጁ ያለበትን የመማሪያ ክፍሎች ጥበት ለመፍታት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የማስፋፋያ ግንባታ እያካሄደ ነው። በምረቃ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የዞኑ ትምህርት ፅህፍፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳ ግዛው ምሩቃን በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በተመደቡበት ቦታ ሁሉ ተግባራዊ በማድረግ ሙያዊያ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በ1972 ዓ ም የተቋቋመው ኮሌጁ እስካሁን ድረስ ከ52ሺህ የሚበልጡ መምህራንን በሰርትፍኬትና በድፕሎማ መስመረቁ ታውቋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም