ከዕጅ አይሻል…

94

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

ጥንት በድንጋይ ዘመን አባቶቻችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውና ተግባራቸውን ለመከወን ሁሉ ነገራቸውን በዕጃቸው፤ ከፍ ሲልም በመሳሪያ በመታገዝ ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር የዝግመተ ለውጥ ታሪክ  ያስረዳል። እንዲያም ሆኖ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ላሰቡበት አላማ ሳይውልና ሲልፈሰፈስ  “ከዕጅ አይሻል ዶማ” በማለት ይገልጹታል። የአባባሉ መነሻ ሀሳብ አንድ ነገር  ለተቋቋመለት አላማ መዋል ሲያቅተው የሚጠቀሙበት አገላለጽ ነው።

በዚህም በመታገዝ ህዝቦች የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን በመግፋት አሁን የግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ ደርሰናል። የአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ መለኪያዋ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃን እና ጥቅል አገራዊ ገቢ (GDP) መሰረት ያደረገ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በመሆኑም በኢትዮጵያ መንግስት ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ድህነትንና ኋላቀርነትን ከሀገራችን ለማስወገድ፣ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ ተግባርም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ጠንካራ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ የግብርና መር ኢንዱስትሪ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ ቢሆንም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል አልተቻለም፡፡

በዕለታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው መረን የለቀቀ የዋጋ ጭማሬ መታየቱ ለዚህ እንደማሳያ የሚቀርብ አገራዊ ችግር ነው። መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት መሰረታዊ ፍጆታዎችን በድጎማ መልክ እያቀረበ ቢሆንም፤ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ የኑሮ ውድነት በየዕለቱ እየጨመረ ሰዎች ነገን ከማለም ዛሬን ለመኖር እየተፍጨረጨሩ የዋጋ ግሽበት እያንገላታቸው ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያው በገበያው ላይ እየታየ ያለው አንድ ኪሎግራም ቀይ ሽንኩርት ዋጋ በ28 ብር መሸጥ አንዱ ነው።

ምንም እንኳን መንግስት በነደፈው ነፃ የገበያ ሥርዓት ሀገራችን የተቀበለችውን የዓለም አቀፍ የኀብረት ሥራ ማህበራት መርህ ቢተገበርም በበርካታ ምክንያቶች የሚፈለገውን ያህል የኑሮ ውድነቱ ዚቅ ሊል አለመቻሉ ከሸማቾችና ንግድ ውድድር ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። በአገር አቀፍ ደረጃ የኅብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ አንዱ የልማት አማራጭ ከመሆኑም በላይ ሸቀጥን ከአምራቾች በመረከብ በዝቅትኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማከፋፈል እየተፈጠረ ያለውን አገራዊ የኑሮ ውድነት መቅረፍ በአዋጅ ቁጥር 895/2009 የተሰጣቸው ዋነኛ ተልኳቸው ነው። በዚህም ዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታትና ያለባቸውን የጋራ ችግር በጋራ ለመወጣትና የገበያ ዋጋ መናርን ለመከላከል የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተዋል፡፡

በአንድም በሌላም ምክንያት እነዚህ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት የተጣለባቸውን አገራዊ አደራና በአዋጅ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ሙሉ በሙሉ እየተወጡ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጄንሲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች የስራ እንቅስቃሴና ችግሮች ላይ ያስጠናው ጥናት ያስረዳል። እንደ ጥናቱ ግኝት በአገሪቱ ወደ 82 ሺ የሚጠጉ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ቢኖሩም አሁን እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት መቅረፍ ብሎም መቀነስ እንዳልቻሉ ያሳያል።

እንደ ጥናቱ ግኝት ከሆነ እነዚህ በተለይ በከተሞች አካባቢ ቁጥራቸው በርከት ባሉ ነዋሪዎች የተደራጁት 146 አካባቢ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ ሲያከናውኑ አይታዩም።  ከችግሮች መካከል አንዱ ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መዋሉና ዋጋ በአድማ እየተወሰነና የምርቶች ሥርጭት ሥልታዊ በሆነ መንገድ እየተስተጓጎለ ስለመሆኑ ተገልጿል።  ከአምራች ወይም ከአስመጪ እስከ ችርቻሮ ንግድ ድረስ ያለው መጠኑ የበዛ ሰንሰለት በፍላጎትና በአቅርቦት ሕግ መተዳደር ያለበትን ጤናማ ግብይት ጤና እያሳጣው እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ።

ሌላው በጥናቱ የተዳሰሰው ምክንያት ደግሞ የሸማቾች ህብረት ስራ የአቅም ማነስና ዩኒየኖች በተደራጀ መልኩ ያለመስራት እና የግንኙነቱ ሰንሰለት መላላት አንዱ ነው። በዚህ ምክንያትም ማህበራቱ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየሰሩት ያለው ተግባር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በሌላ በኩል ሕዝቡን ከአልጠግብ ባዮች ይታደጋሉ የተባሉ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትና በመንግሥት የተቋቋሙ የማከፋፈያ ድርጅቶች ጥቅም ግልጽ እየሆነ አይደለም፡፡

እነዚህ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በዓለማችን በተለይም በአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትሎ በተፈጠረው የኑሮ ቀውስ ለመፍታት በመደራጀት ግንባር ቀደም ችግር ፈች መሆናቸውን ከአለም አቀፍ ህብረት ስራ ማህበር ኤጄንሲ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የህብረት ሥራ እንቅስቃሴ በተደራጀ፤ ዘለቄታ ባለውና ዘመናዊ አሠራሩን በተከተለ መልኩ የሚፈፀም አልነበረም። የኢኮኖሚ ምሁራን በእንግሊዛውያኑ ሮበርት ኦውንና ዊልያም ኪንግ እንዲሁም በፈረንሳዊው ቻርለስ ፎሪየር አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የህብረት ሥራ እንቅስቃሴና አስተሳሳብ እንዲፈጠር አስችለዋል።

ስለ ዘመናዊ የህብረት ሥራ ማህበራት መቋቋም ስንቃኝ ግን በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበር ዕድሜ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ማስቆጠሩን እንገነዘባለን። የህብረት ሥራ ማህበራቱ በህግ መቋቋም የጀመሩት በንጉሡ ዘመን ሲሆን፤ መጀመሪያ ጊዜም የገበሬዎች የእርሻ ህብረት ሥራ ድንጋጌ በ 1953 ወጥቶ ሥራ ላይ ውሏል። አሁን በአገራችን እየታዬ ያለው የኑሮ ውድነት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ወይም ሌላ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ ከሚያደርጉ ነጋዴዎች ጋር በመግባባት ስርዓት ባለው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ናቸው።

ከተሞች ላይ የዳቦ ስንዴ አቅርቦት ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ በተከታታይ እንዲቀርብ እየተሠራ ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስንዴ 4 መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን መገዛቱንና ስኳር 614 ሺህ 222 ኩንታል እየተሰራጨ እንደሆነ ገልጸው፤ ተጨማሪ እንዲገባና የገበያ ማረጋጋቱን ሥራ እንዲደግፍ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

እነዚህ ዋጋን በማረጋጋት የምርቶችንና የሸቀጦችን ሥርጭት ፍትሐዊ ያደርጋሉ የተባሉ ተቋማት ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሲከላከሉ አይታዩም። ብዙዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ እየሳቱ በአልጠግብ ባዮች በመጠለፋቸው ከዕጅ አይሻለ ዶማ አይነት ተግባር ውስጥ ተዘፍቀዋል። ሕዝቡን አስመራሪ ከሆነው የኑሮ ውድነት ሊታደጉት ካልቻሉ የእነሱ ህልውና ምን ይጠቅማል የሚል ሀሳብ ይሰነዘራል።

ሸማቾች በአንድ የኢኮኖሚ ሥርዓት ካሉ የተለያዩ ተዋናዮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ‹‹ፍላጎት›› (Demand) በማለት የሚገልጹትን ሐሳብ ከሚወክሉት ውስጥም ይመደባሉ፡፡ ይህም ማለት ሸማቾች በንግድ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ወደ ገበያ የሚቀርቡትን የተለያዩ ዕቃዎችና አግልግሎቶች የሚገዙ ናቸው።

የአገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ባደጉ አገራት በተለይ በአሜሪካ የፍጆታ ዕቃ ዋጋ ሲጨምር ፍላጎታቸውን በመቀነስ ሸማቹ በራሱ የዋጋ ንረቱን ያረጋጋል። ለዚህ ማሳያው የነዳጅ ዋጋ ሲንር የቤተሰቡ አባላት በየግሉ ይጓዝበት የነበረውን መኪና በማጠፍ እና አንድ ወይም ሁለት መኪና ብቻ በመጠቀም ፍላጎታቸውን ይቀንሳሉ። በዚያም አቅርቦቱ በብዛት ሲጨምር እና ፍላጎት ሲቀንስ የግድ ዋጋ ሳይወድ በግድ ይቀንሳል። ሌላው ነጻ ገበያን ፖሊሲ የሚከተሉ አገራት ምክንያታዊ ያልሆነ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ሲያጋጥም በመንግስት ደረጃ ህብረተሰቡን የማንቃትና የማስጠንቀቅ ተግባር ይሰራሉ።

በዚህም በቺካጎ ዊሊያም ሬኒ ሀርፐር ኮሌጅ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የዋጋ ግሽበት የሚከሰተው በሁለት መንስኤዎች መሆኑን ያስረዳሉ፤ ‹‹ፍላጎት ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ እና አቅርቦቱ ዝቅተኛ ሲሆን የዋጋ ግሽበት ይከሰታል›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ይልቅ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸው ምርቶች ስለሚበዙ የንግድ ልውውጥ አለመመጣጠን እንዳለም ፕሮፌሰር ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ ከውጭ ገዝቶ ለማምጣት የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም ኢትዮጵያ ግን የገንዘቡ እጥረት አለባት፤ ባለው የውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የሚመጣው ምርትም ወደ ሀገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ ሲመነዘር የመሠረታዊ ሸቀጥ ምርቶች ውድ እንዲሆን እያደረገ ነው ሲሉም ፕሮፌሰር ጌታቸው አብራርተዋል።

ምንም እንኳን በሃገራችን ያለው የገበያ ሁኔታ ውድድር ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ቅጥ ያጣ እንደሆነ በርካቶች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት በፍጆታ ዕቃዎችና በግብርና ምርቶች አቅርቦት እየደረሰ ያለውን የመጠን፤ የጥራትና የመለኪያ ችግሮች የዋጋ ንረት በመከላካል ፍትሐዊ የግብይት ስርዓት እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። የንግድ ሥራ ራስን የምንጠቅምበት ሥራ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የምናገለግልበት ጭምር ነው። ስለዚህ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራ የንግዱ ማህበረሰብ ሁሉ ከሚያገኘው ትርፍና ኪሳራ ጀርባ የሚያገለግለው ወገንና ህዝብ መኖሩን ማገናዘብና ለአገሩ ዕድገትና ሠላም የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ አገራዊ ግዴታ ነው፡፡

ይሄን ችግር ለመቅረፍ የሚመለከታቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎችና የንግድ ሚኒስቴርም እንዲህ አይነት ጭማሪዎች ሲከሰቱ ጊዜ ሳይሰጥ ችግሩን መፈተሽና የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። በተለይ አላግባብ የዋጋ ሸቀጦችን የሚደብቁና የዋጋ ንረት እንዲከሰት የሚያደርጉ፣ በገበያ አካባቢ የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚነዙ፣ በአቋራጭ ለመክበር ሲሉ ከልክ በላይ ዋጋ የሚያንሩ እና መሰል ሁከት ፈጣሪዎችን ተከታትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል።

ይህ ካልሆነ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የሚከሰተው ችግር ሁሉንም የሚጎዳ ነው፡፡ በተለይ አሁን በተፈጠረው ሠላም ፊቱን ወደ ልማት ለማዞር ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ የሚገኘውን ዜጋ በዚህ ችግር ተጠልፎ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዳያሳድር ፈጣን ምላሽ መስጠት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።

በጥቅሉ ይህ ለነገ የማይባል፣ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ህይወት የሚነካ፣ በተለይም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የመኖር ሕልውናን የሚፈታተን የህገወጦች ጉዳይ መስመር ከማስያዝ ባሻገር፤ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ የምጣኔ ሃብት ምሁራንን በማማከር ለተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና አገራዊ የዋጋ ግሽበት አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ ለማሰጠት፤ በተለይ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በአዋጅ የተሰጣቸውን ገበያውን የማረጋጋት ተግባር ሊወጡ ሲችሉ ነውና  ጊዜው አሁን ሊሆን ይገባል በሚል መንፈስ መስራት ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም