የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

68
ሰኔ 17/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ልዩ ተወካይ ሚስተር ኤርሊንግ ስኮይንስበርግ ጋር ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተወያዩ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላችው መሆኑን በማስታወስ በቀጣይ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን  ገልጿል። በሱዳን የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተጫወተች ያለውን ሚና ልዩ ተወካዩ አድንቀዋል። በተጨማሪም በደቡብ ሱዳን በዋነኞቹ ኃይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተግበራዊ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ሁሉቱ ባለስልጣናት ውይይት ማድረጋቸውም ተመልክቷል። በዚህ ረገድ ኖርዌይ እያደረገች ያለውን ድጋፍ በተለይም የልዩ ተወካዩን አስተዋጽኦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አድንቀዋል። በሌላ በኩል ከ70 በላይ የኢትዮጵያና ኬንያ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የተሳተፉበት የንግድና ኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ ትናንት በኬንያ መዲና ናይሮቢ መካሄዱን በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። አውደ ርዕዩ በዓይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነና በአውደ ርዕዩ በሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ቱሪዝም መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ የሚያተኩር የግማሽ ቀን የፓናል ውይይትም መካሄዱ ተገልጿል። የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ በተወካያቸው አምባሳደር ጆንሰን ዌሩ አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት የኬንያና የኢትዮጵያ መንግስታት በአገራቱ መካከል የተሳለጠ የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ እንዲኖር ተባብረው መስራት አለባቸው ብለዋል። በመሪዎቻችን ከተፈጠሩ መልካም አጋሚዎች በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አንዱ የሌላውን ምርትና አገልግሎት የመጠቀም ባህል እንዲዳብር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችንም ኬንያውያን ባለሃብቶች በደንብ እንዲጠቀሙባቸውና ኢንቨስት እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያና ኬንያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሕዝቦችን ሕይወት ሊቀይሩ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን አንስተው ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ወደላቀ አጋርነት ለማሸጋገር እንደምትሰራ ጠቅሰዋል። የኬንያ ባለኃብቶች ወደኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ኢትዮጵያ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ በተለይም በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት፣ በኢነርጂና በቴሌኮሚዩኒኬሽን ዘርፎች እየመጡ ያሉ ሪፎርሞች የዚሁ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል። የንግድና ኢንቨስትመንት አውደ ርዕዩ ዓላማ በኢትዮጵያ ያሉ ዘርፈ ብዙ የቢዝነስ መልካም አጋጣሚዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ በሁለቱ ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ አባላት ዘንድ ትስስር ለማመቻቸት፣ የሀሳብ መለዋወጫ መድረክ ለመፍጠር እንዲሁም በተለያዩ በመንግስትና ባለሀብቶች መካከል ያለውን ግንኙነትና ተባብሮ የመስራት ባህል ለማጠናከር እንደሆነም አምባሳደር መለስ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም