በደቡብ ክልል በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ224 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተከሉ

69
ሐዋሳ ሰኔ 21/2011 በደቡብ ክልል በዘንድሮው ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ224 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ምክትልና የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ መና እንደተናገሩት ችግኞቹን የተተከሉት ከተዘጋጀው 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞች መካከል ነው። በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ በሚተገበረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ባለፉት የበጋ ወራት 360 ሺህ ሄክታር ላይ የአፈርንና እርጥበትን የሚያስጠብቁ የእርከን ሥራዎች ፣ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችና መሰል  ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ተከላው እፅዋቶችና የጥላ ዛፍ ችግኞች እንደሚያካትት  አቶ መለሰ ተናግረዋል። ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲጀመር የክልሉ የደን ሽፋን 19 በመቶ እንደነበር ያሰታወሱት አቶ መለሰ በእቅዱ ማጠናቀቂያ 25 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት የተተከለው ችግኝ የፅድቀት መጠን ጥናት በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች 78 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ መቻሉን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ የጽድቀት መጠን 85 በመቶ ለማድረስ መስራቱን  አስረድተዋል። የስልጤ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ምክትልና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ፈርጌሳ በ42 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ላይ ለችግኝ ተከላ የሚሆን ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። ዞኑ 102 ሚሊዮን ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፍራፍሬዎች፣ የመኖ እፅዋትና ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጠቀሜታ ያላቸው የአገር በቀል ዛፎች ችግኞች መከናወናቸውን አስረድተዋል። ከሚያዚያ 2011 ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የችግኝ ተከላ ስራ 19 ሚሊዮን 750 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል። ባለፉት ስምንት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ተግባራት የዞኑን የደን ሽፋን መጠን ከአራት በመቶ ወደ 16 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። የባለፈው ዓመት የችግኝ የጽድቀት ተከላ መጠን 79 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው በዚህ ዓመት የሚተከሉትን ችግኞች የጽድቀት መጠን ወደ 97 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። የስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ አርሶ አደር ፈዲላ ደምሴ በአካባቢው በበጋ ወቅት በተከናወነው የእርከን ሥራ መሬቱ ማገገሙን ገልጸዋል። "ከእንግዲህ አካባቢያችንን ለማልማት የአመራር አካላትን ቅስቀሳ አንጠብቅም" ብለዋል ፡፡ ሌላዋ የዚህ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገነት ባለኬር ባለፈው ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የከብቶች መኖን ጨምሮ ከ600 በላይ የፍራፍሬ፣ የቡናና የጥላ ዛፍ ችግኞችን  መትከላቸውንና መኖ ማልማታቸውን ተናግረዋል። በተለይም መኖውን ለከብቶቻቸው ፍጆታ ከማዋል ባለፈ በወር ከሶስት ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት ከ500 በላይ የፍራፍሬና ቡና ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ፡፡ በደቡብ ክልል ከሚተከሉት ችግኞች 70 በመቶው የቡና ፤ ፍራፍሬና የጥላ ዛፍ ሲሆኑ፣ 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለመኖ የሚሆን ሳርና ሌሎች እፅዋትን እንደሚያካትት ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም