ከእምቦጭ አረም ኢታኖልና ናፍጣን ጨምሮ የቤተ ሙከራ ኬሚካሎችን ማምረት ይቻላል- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ

89
ጎንደር ሚያዚያ 28/2010 ከእምቦጭ አረም ኢታኖልና ናፍጣን ጨምሮ የቤተ ሙከራ ኬሚካሎችን ማምረት እንደሚቻል ባካሄደው ምርምር ማረጋገጡን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 28ኛው ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ ተጠናቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ እንደተናገሩት ተቋሙ አረሙን በሳይንሳዊና ስነ-ህይወታዊ ዘዴዎች ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አጋዥ ምርምሮች ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በተጓዳኝም አረሙ አማራጭ የኢነርጂ ኃይል ምንጭ እንዲሆን በማድረግ በኩልም ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ሦስት ዓመታት ባደረገው ምርምር ናፍጣና ኢታኖል ከአረሙ ሊመረት እንደሚችል በቤተ-ሙከራ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በባዮሎጂና በኬሚሲትሪ ዘርፍ ለቤተ-ሙከራ ሥራ የሚያገለግሉ "ሰልፈሪክ እና አሴቲክ አሲድ" የተባሉ የኬሚካል ግብአቶችን ከአረሙ ማግኘት እንደሚቻል ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ምርምር ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከአረሙ ያገኘውን 250 ሊትር ናፍጣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ትክክለኛነቱን ማረጋገጫ ከማግኘቱም በላይ ከኢትዮጵያ የአዕምሮአዊ ንብረት ድርጅትም የባለቤትነት መብት የምዝገባ ሰርተፊኬት መቀበሉን አስታውቀዋል። እንደፕሮፌሰር መርሻ ገለጻ፣ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ ከአፈርና ከእንስሳት ተረፈ ምርት ነዳጅን ከማምረት ጀምሮ ዳጉሳን ለቢራ ጠመቃ ስራ በማዋልና የአለቁ የላፕቶፕ ባትሪዎችን ዳግም ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል የፈጠራ ግኝቶች ባለቤት ነው። በተጨማሪም የፋብሪካ ምርቶችን የሚተካ የኮላ ማጣበቂያና የጥርስ ሳሙናን በምርምር ማፍለቁንና 11 የምርምርና የፈጠራ ሥራዎቹን በኢትዮጵያ የአዕምሮአዊ ንብረት ድርጅት በባለቤትነት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ ለችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በቂ በጀት ከመመደብ ጀምሮ ለተመራማሪዎች የማትጊያ ስርአት ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ናቸው፡፡ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ዩኒቨርሲቲው በመደበው 35 ሚሊዮን ብርና ከአጋር አካላት በተገኘ 152 ሚሊዮን ብር 109 የምርምር ፕሮጀከቶች መከናወናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። "ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎችን ተደራሽ በማድረግ በኩል 9 የምርምር ማዕከላትን በሰሜን፣ በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በማቋቋም ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ ምርምሮችን እያካሄደ ነው" ብለዋል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎቻቸውን ለማህበረሰቡ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ልክ ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያከናውናቸው ምርምሮች አበረታች መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚያካሂዷቸው የምርምር ሥራዎች በሚኒስቴሩ በኩል የቅርብ እገዛና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረታቸውን ያደረጉ ከ70 በላይ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል በምርምር ኮንፍረንሱ ላይ በሀገሪቱ ከሚገኙ 20 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን ጨምሮ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ተካፋይ ሆነዋል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም