በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት ሳንከፋፈል በሃገራዊ ጉዳዮች ተደጋግፈን እንሰራለን…የሃዋሳ ነዋሪዎች

78

ሃዋሳ ሰኔ 19/2011በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶቻችን ሳንከፋፈል በሃገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ተደጋግፈን እንሰራለን ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎች ሰሞኑን በሀገር መከላከያና በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመውን ግድያ አውግዘዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ ተሰማ አቦሴ በአማራ ክልልና በመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ላይየተፈፀመው ግድያ እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ድርጊቱ ለሀገር እድገትና ለህዝቦች አንድነት እየለፉ ባሉ መሪዎች ላይ መፈጸሙ አንገት የሚያስደፋ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትታወቀው የውጪ ወራሪዎችን በተባበረ ክንድ አሳፍራ በመመለስ እንጂ ወንድም በወንድሙ ላይ ጨክኖ በመገዳደል ታሪክ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

“አሁንም ተባብረን በየአካባቢያችን ያሉ ጥፋተኞችን ለህግ አካላት አሳልፈን በመስጠት ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገባል” ያሉት አቶ ተሰማ መንግስትም የህግ የበላይነትን ለማስፈን የእርምት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

አቶ አለማየሁ ጎዴቦ የተባሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የመሪዎች መሞት በሀገር ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል የማይባል እንደሆነ ተናግረዋል።

“ከአሳዛኙ ክስተት በኋላ መሪዎቻችን ያሳዩት አለኝታነትና ያንፀባረቁት ሀገራዊ አቋም እኛንም ተስፋ ከመቁረጥ ታድጎናል”ያሉት አቶ አለማየሁ ዳግም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት አመራሩም ሆነ ህብረተሰቡ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“በብሔር ማንነትና በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ሳንከፋፈል ልዩነቶቻችን አንደተጠበቁ በሀገራችን ጉዳይ ተደጋግፈን መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ክስተቱ ሁሉንም ኢትዮጰያዊያንን ያሳዘነ እንደሆነ ገልጸው መንግስት በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለይቶ በአፋጣኝ ለህግ ማቅረብ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አለማየሁ ሀዳሞ ናቸው።

በጉዳዩ ዙሪያ መረጃዎችን አዛብቶ በማሰራጨት ህዝቡ ሌላ ግጭትና ቀውስ ውስጥ እንዲገባ የሚጥሩ ሃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው የተጣራ መረጃ በወቅቱ ለህብተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በሀገር ጉዳይ ላይ ሁሉም ህብረተሰብ እኩል ተቆርቋሪ መሆን እንዳለበት ገልጸው እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በውስጡ የሚደበቁ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።