የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን አወገዙ

66
ነቀምቴ ሰኔ 19/2011በምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የአገሪቱን ጸጥታና ሰላም የሚያውኩና ግድያ እየፈፀሙ ያሉ አካላትን በተቃውሞ ሰልፍ አወገዙ። ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል በዞኑ የኑኑቁምባ ወረዳ ነዋሪ አቶ ነጋሽ አዱኛ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በአማራ ክልልና በሀገር መከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ የሟቾች ቤተሰቦችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያንን ህዝብ ልብ የነካ ነው"። ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በውይይት መፍታት እየተቻለ ከፍተኛ አመራሮችን በመግደል የግል ፍላጎትን ለማሳካት መሞከር ጊዜው ያለፈበት አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በጥብቅ እንደሚያወግዙም አመልክተዋል። የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ቀጣይነት እንዳይኖረውና የህብረተሰቡን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና፣ የመከባበር ባህል ለማደቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ከመንግስት ጎን ቆመው ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የጅማ አርጆ ወረዳ ነዋሪው አቶ ወጋሪ ታደሰ በበኩላቸው ከህዝቡ ፍላጎት ውጪ እኔ ላንተ አውቅልሀለው የሚሉና የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከመካከላቸው በማውጣት ለህግ ለማቅረብ እንደሚሰሩ አመልክተዋል። መንግስት በአማራ ክልልና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ግድያ የፈጸሙና ተባባሪዎቻቸውን ለህግ እንዲያቀርብና ትክክለኛውንመረጃ ፈጥኖ ለህዝቡ እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል። አቶ ወጋሪ እንዳሉት በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግዱና የአገሪቱን ሰላም የሚያውኩ አካላትን ከህብረተሰቡ ነጥሎ በማውጣት ወደ ህግ ለማቅረብ ህብረተሰቡ ዝግጁ መሆኑን በሰልፉ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አየለች ታደሰ በዞኑ በሚገኙ 12 ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በአማራ ክልልና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም ዛሬ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል። በከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያወገዙት ኃላፊዋ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ ማገዝ እንዳለበት አመልክተዋል። የተቃውሞ ሰልፉ በዞኑ ሊሙ፣ በሃሮሊሙ፣ በኢባንቱ፣ በዋዩቱቃ፣ በኑኑቁምባ፣ በጅማ አርጆ፣ በኪረሙ፣ በሳሲጋ፣ በቦያ ቦሼ ፣ በሌቃ ዱለቻ፣ በዋማ አገሎ ወረዳዎችና በአንገር ጉቴ ከተማ መካሄዱ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም