ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አገራዊ አመለካከትን መፍጠር እንደሚገባ የኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ገለጹ

93
ጭሮ/ጅማ/ደብረ ብርሃን ሰኔ 19 / 2011 ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን መሆን አንድ አገራዊ የጋራ አመለካከትን መፍጠር እንደሚገባ የኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርስቲ ተማሪያዎችና መምህራን ተናገሩ። የዩኒቨርሲቲው አንዳንድ መምህራንና ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ጠንካራ ባህልን በማዳበር ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገነባል። በዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መምህር ነጂብ ቃሲም በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲንቀሳቀስ አስታውቀዋል። ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መንግሥት ሕዝቡን ያማከለ ፖሊሲ ቀርፆ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል። በዩኒቨርሲቲው ሌላው መምህር የሱፍ ዓሊ በበኩላቸው በአገሪቱ የተገኘው ለውጥ በተለይምወጣቱ በከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት አስታውሰዋል። አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት ከተግባራቸው ተቆጥበው የተሻለች አገርን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል። በዩኒቨርስቲው የሁለተኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ሙባሪክ ቶፊቅ፤ ዜጎች የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሂደት ለማጠናከር ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክቷል። በአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች የተፈጸመው ግድያ የአገሪቷን ለውጥና ሰላም የማይሹ ግለሰቦችን ማንነት በግልፅ አሳይቷል ያለው ሙባረክ፣ በአገሪቱ የፈጠነቀው የተስፋ ብርሃን እንዳይደበዝዝ ድርጊቱን እንደማንቂያ ደወል ልንጠቀምበት ይገባል ብሏል። በዩኒቨርስቲው የሦስተኛ ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ተማሪ ማህደር በላይ በበኩሏ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንዳለበት ተናግራለች። ኅብረተሰቡ የሚገጥመውን ተግዳሮቶች በማለፍ ለአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁማለች። በተመሳሳይ በከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመው የግድያ ወንጀል የአገራችንን መልካመ ምስል ና ስም የሚያጎድፍ በመሆኑ እናወግዘዋለን ሲሉ በጅማ ዞን የአጋሮ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ከከተማው ከአምስት ቀበሌዎች የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ነዋሪዎች አቋማቸውን የገለፁት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዛሬ በተተወያበት ወቅት ነው ። ነዋሪዎቹ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በአማራ ክልልና በመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈመውን ግድያ አውግዘዋል። ''በአመራሮቹ ላይ የተፈመው የግፍ ግድያ ከግለሰቦች ባለፈ ሀገሪቱን የጎዳ በመሆኑ ድርጊቱን በፅኑ እንቃወማለን” ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል ። የከተማው ከንቲባ አቶ ኤልያስ ሸረፎ በበኩላቸው በከፍተኛ አመራሮች ላይ የተከሰተውን ድርጊት ከማውገዝ ባሻገር መታገልም ያስፈልጋል ብለዋል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ዞን አገረ ስብከት፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን ኅብረት፣የደብረ ብርሃን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፣ የሰሜን ሸ ዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤትና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ማህብረሰብ በድርጊቱ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፤ ዜጎች አገራዊ ለውጡን ለማራመድ የጀመሩትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናከሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም