"የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲሲቱ የተስፋ አድማስ ማድረግ እንጂ የሀዘን ማቅ ማልበስ አይደለም" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

120
ሰኔ 18/2011 "የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲሲቱ የተስፋ አድማስ፣ የአፍሪካ ፈርጥና ተምሳሌት ማድረግ እንጂ የሀዘን ማቅ ማልበስ አይደለም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በባህርዳርና በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦርና የሲቪል አመራሮች ግድያ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለመከላከያ ሰራዊቱ፣ ለሟቾች የስራ አጋሮችና ለሟች ቤተሰቦች የሀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲሲቱ የተስፋ አድማስ የአፍሪካ ፈርጥና ተምሳሌት ማድረግ እንጂ ኢትዮጵያን የሀዘን ማቅ ማልበስ አይደለም ብለዋል። አገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እስከተረዳን ድረስ እየመረረንም ቢሆን የምንቀበለው ሀሳብ ቢኖርም በአገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዘላቂ ጥቅምና ክብር ላይ ግን ድርድርም ሆነ ትዕግስት ፈጽሞ አይኖረንም ብለዋል። ከኢትዮጵያ የሚበልጥ፣ ከሕዝብ የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ ተናግረው "ለዴሞክራሲና ለሰላም ስንል እንታገሳለን፤ ለአገርና ለሕዝብ ስንል መራር ውሳኔን እንወስናለን" ብለዋል። አንድ ዓመት ባስቆጠረው አገራዊ የለውጥ ጉዞና የመደመር ጎዳና ላይ እያለን በጓዶቻችን ላይ የተፈጸመው ልብ ሰባሪ ጥቃትና አገራችን የገጠማትን ብርቱ ፈተና ስናስብ ልባችን በከፍተኛ ሀዘን የሚደማው ያለ ምንክንያት አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዘን መግለጫቸው። እነዚህ ሰማዕታት እንደ አለት የጸኑ፣ እንደ አልማዝ የጠነከሩ፣ አገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የማገልገል አላማን ያነገቡ፣ ዓላማቸውን ሳያሳኩ አንገታቸውን ላለማዞር የቆረጡ ይህንንም በተግባር ያረጋገጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደሆኑም ገልጸዋል። "ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የፖሊስ ሃይላችን እና የጸጥታ አካሎቻችን እዝና ተወረዳቸውን በላቀ ወታደራዊ ስነ ምግባር ጠብቀው ተልዕኳቸውን በከፍተኛ ደረጃ በመወጣት አኩሪ ገድል በመፈጸም ዛሬም እንደ ትናንቱ እንድንኮራና እንድንመካባቸው አድርገዋል" ብለዋል። በዚህም የተሰማቸውን ክብርና ለእነርሱም ያለቸውን አድናቆት በመግለጽ በዚሁ ህዝባዊ ወገንተኝነት አገራዊ ሃላፊነታቸውን በቀጣይነት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አስተላልፈዋል። "በየዘመናቱ እኩያን እየተነሱ ከመንገዷ ሊጎትቷት፣ከግስጋሴዋ ሊመልሷት፣ከክብሯ ሊያዋርዷት ሲዳዳቸውና ሲውተረተሩ ዝም ብላ አታውቅም " በማለት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያም ቢሆን ኢትዮጵያ እንደገና እየተነሳች እንደገናም እየገሰገሰች እንደገናም ወደ ገናናነቷና ወደ ክብሯ ዛሬ ላይ እንደደረሰች፤ ይህንንም እናቶቻችንና አባቶቻችን ትተውልን ያለፉት ቅርሶች ይህንን ሃቅ ደጋግመው ነግረውናል ብለዋል። "ኢትዮጵያ ቀጥና የማትበጠስ ተዳፍና እሷቷ የማይጠፋ ተናግታ የማትፈርስ ተናውጣ ስሯ የማይበጠስ አገር ናት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ አክባሪ ዜጎቻችን ደግመው ደጋግመው በተለያዩ መድረኮች የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ሲመክሩ በጥሞና አድምጠናል ብለዋል። "መግደል መሸነፍ ነው ስንል የሀሳብና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሉዓላዊ ሀሳብ እንጂ በጥይት ማሸነፍ እንደማይቻል በመረዳት ነው" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የጠቀሱት። "መግደልና መገዳደል ጦርነትና ግጭት አገርን መቀመቅ ውስጥ እንደሚከት ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚረዳው እንደሌለና ውረድ እንውረድ ግደል ተጋደል የት እንዳደረሰን ከኛ በላይ ምስክር የለም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ዓላማቸው ሶስት ነገሮችን ማስከተል እንደሆነ በግልጽ እንደሚታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫቸው አንስተዋል። በአንድ በኩል የለውጡን ሐዋርያት በመግደል ለውጡን ለማስቆም፣ በሌላ በኩል ህዝባችንን በተሳሳተ ምስል እርስ በእርሱ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ማድረግ፣ በሶስተኛ ደረጃም የጸጥታ አካሎቻችንን ሞራልና ከብር በመንካት እና አንድነቱን በጎጥ በመከፋፈል አገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነበር ብለዋል። ግን የታሰበው አላማ አልተሳካም "የኢትዮጵያ አምላክ ለቅዠታቸውና ለእኩይ ተግባራቸው አሳልፎ አልሰጠንም ወደፊትም አይሰጠንም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በአገሩና በወገኖቹ ጥቃት የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአባቶቹ አንደለመደው ከአገሩ ልጆች እና ከጀግኖቹ ጋር በአንድነት በመቆም ክፉውን ሴራ አክሽፎታል ብለዋል። በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ፖለቲከኞቻችን በአብሮነትና በጽናት በመቆም ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሬ ወርቅ ተፈትኖ እንደ ጥሩ ወርቅ ነጥሮ እንደሚወጣ ዳግም ለዓለም አረጋገጠዋል ሲሊም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሩት። እያለቀስን ብንቀጥል የጓዶቻችንን ዓላማ አናሳካም ተስፋ ብንቆርጥ የጓዶቻችንን ሰንደቅ ከፍ አናደርገውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን እንዲህ ሆነ? ድክመታችን ምን ነበር? ምንስ ማድረግ ነበረብን? የሚሉትን ጉዳዮች በትክክለኛ ጥናት እንለያለን ብለዋል። ካጋጠመን ፈተና እንማራለን አንዳይደገም አድርገን ህገ ወጥ በሮችን ሁሉ እንዘጋለን በማለትም ለአፍታም እንኳን ከጉዟችን እንገታም ከዓለማችን አንዛነፍም መንገዳችንን አንቀይርም ሲሉ አረጋግጠዋል። በፈተናችን ወቅት ከጎናችን በመቆም ድጋፋችሁና ማጽናናታችሁ ላልተለየን ወዳጅ አገራት በራሴና በመንግስት ስም ምስጋዬን አቀርባለሁም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዘን መግለጫቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም