"ኢትዮጵያ ለአገራቸው ከባድ መስዋዕትነት የከፈሉ ባለውለታ ልጆቿን አጥታለች" - አቡነ ማትያስ

57
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2011 ኢትዮጵያ ለአገራቸው ከባድ መስዋዕትነት የከፈሉ ባለውለታ ልጆቿን አጥታለች ሲሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተቀነባበረ ሴራ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ህይወታቸውን አጥተዋል። የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ የአስከሬን ሽኝት ስነ-ስርዓትም ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። በስነ-ስርአቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና የሟች ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ ተገኝተው ሽኝት አድርገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሰውን ያለምክንያት መግደል የሚያስኮንንና የሚያስፈርድ ከመሆኑም ባሻገር በመንፈሳዊም ሆነ በስጋዊ አስተምህሮ ፍጹም የተወገዘ ነው። የተሰዉት የመንግስት አመራሮችና ጄኔራሎች ለአገራቸው በርካታ መስዋዕትነትን የከፈሉና አገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ ንጹሃን ዜጎች ናቸውም ብለዋል። አገራቸው በሰላምና በልማት ጎዳና እንድትጓዝና ህዝቦቿ ከድህነት እንዲላቀቁ ያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ታላላቅ ባለውለታ ልጆቿን አጥታለች ያሉት ፓትርያርኩ የተሰዉት ሰማዕታት በሰሩት አኩሪ ስራ ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል ሲሉ ተናግረዋል። በሰከነ መንፈስ በመነጋገርና በመወያየት እንጂ በመገዳደል የሚጠፋ ችግር እና የሚመጣ ለውጥ አይኖርም በማለት፤ የተፈጸመው ተግባር የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገን አጸያፊ ተግባር ነው ብለዋል። በመሆኑም ሃዘኑ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ አገሪቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማሳደግ በሰላምና በፍቅር ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአቶ ምግባሩ ከበደ እና የአቶ እዘዝ ዋሴ የቀብር ስነ-ስርአት ነገ ከቀኑ ሰባት ሰዓት በባህርዳር አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የሚፈጸም ሲሆን የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ቀብር ደግሞ ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በመቀሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም