በባህርዳርና አዲስ አበባ የተፈጸመውን የወንጀል ተግባር የሚያጣራ ምርመራ ቡድን ስራ ጀመረ

133

ሰኔ 17/2011 በአማራ ክልል ባህርዳር ና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል የሚያጣራ ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ቡድን ተቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

በአማራ ክልል ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ና የአደረጃጀት አማካሪያቸው አቶ  እዘዝ ዋሴ ህይወታቸው አልፏል።

ጥቃት ደርሶባቸው በህክምና ሲረዱ የነበሩት የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደም በዛሬው እለት ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

በዛው እለት በአዲስ አበባ ደግሞ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት ጀነራል ሰአረ መኮንንና ባልደረባቸው ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ  በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።

የፌዴራል ፖሊስ በባህርዳርና በአዲስ አበባ የተፈፀሙትን እነዚህን ወንጀሎች የመመርመር ተግባር መጀመሩን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የምርመራ ስራው የተሳካ እንዲሆን  ህብረተሰቡ ና የፀጥታ  አካላት  ተገቢውን  ድጋፍና  እገዛ  እንዲያደርጉም  የፌዴራል ፖሊስ  ኮሚሽን ኮሚሽነር  ጀነራል እንዳሻው  ጣሰው ጥሪ አቅርበዋል።

ጀነራል ኮሚሽነሩ እንዳሉት የተፈጸመው የወንጀል ተግባር  የህገ-መንግስት ጥቃት፣ የከፍተኛ አመራሮች ግድያ፣ የመግደል ሙከራና አጠቃላይ የመፈንቅለ  መንግስት እንቅስቃሴ ተደርጎ ነው የሚወሰደው።

የወንጀል  ፈጻሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ሙሉ በመሉ በቁጥጥር ስር ለማዋልና የወንጀል ድርጊቱን ለማጣራት የፖሊስ ሰራዊቱ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

የወንጀል ድርጊቱ አስከፊና አገርን ለአላስፈላጊ ብጥብጥ የሚዳርግ የነበረ ሲሆን ፖሊስ  በወሰደው ፈጣን እርምጃ  በአንድ ሰዓት ውስጥ መቆጣጠር ተችሏል።

ድርጊቱ ከተፈጸመ  በኋላ  የክልሉ  የፀጥታ አካላት፣ የአገር  መከላከያ፤ ከመረጃና ብሔራዊ ደህንነት ጋር በመሆን አብዛኞቹ  የድርጊቱን ፈጻሚ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር  ስር  መዋላቸውን አክለዋል።

የተፈጸመው ድርጊት የተልኮ ደረጃ የአጥፍቶ መጥፋት ዓይነት መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ጀነራሉ የተናገሩት።

በባህርዳርና አዲስ አበባ የተፈፀመው ጥቃት የፈፃሚዎቹ  ግንኙነት አንድ  ዓይነትና  ተመሳሳይ ተልዕኮ ያለው  መሆኑን  ያሳየ ነውም ብለዋል።

የወንጀል ተግባሩ “የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ቁንጮ በመምታት  የመከላከያ  እዙን ለመበጣጠስ ታስቦ የተፈፀመ ነው” ሲሉም ኮሚሽነር ጀነራሉ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል መረጋጋት ተፈጥሯል፤ የክልሉ አመራርም ወደ መደበኛ ስራው ገብቷል ያሉት  ኮሚሽነር ጀነራሉ በወንጀል ተግባሩ የተጠረጠሩትን ቀሪ ግለሰቦች ለመያዝ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።