በአማራ ብሄራዊ ክልል የከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ

60
አዲስ አበባ ሰኔ16/2011 የአማራ ክልል "ህዝብ ምልክቶችና ቆራጥ ታጋዮችን በማቁሰል የአንዳንዶቹንም ህይወት እንዲያልፍ አድርገዋል" ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በክልሉ በተፈጸመ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የደረሰውን ጉዳት የገለጹት። የክልሉ መንግስት ለኢዜአ ዛሬ ማለዳ በላከው መግለጫ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወቅት በተፈጸመ ጥቃት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ተሰውተዋል። የክልሉ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥቃቱ ጉዳት ስለደረሰባቸው ህክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል። በፌዴራል መንግስት በተለያዩ ተቋማት የመንግስት የስራ ሃላፊ ሆነው በመሾም ያገለገሉት ዶክተር አምባቸው መኮንን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የሆኑት የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም እንደነበር ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በትናንት ማታ መግለጫቸው በእለቱ በሰዓታት ልዩነት “በአዲስ አበባ ጥቃቱን ለማስቆም ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከቅርብ ሰዎቻቸው ውስጥ በተመለመሉ ቅጥረኞች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል። ይህም በአዲስ አበባና በባህር ዳር ከተሞች የተፈጸመው ጥቃት በተናበባና በተቀናጀ እቅድ መሆኑን አመላካች አድርጎታል። በተቀነባበረና በተቀናጀ ሴራ በተፈጸመ ግድያ ምክንያት የለውጥ ሃይል ከሆኑት መካከል አራት ሰዎች ተሰውተዋል። ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው፣ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ እንዲሁም ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጨርሰው በጡረታ የተሰናበቱት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ መሰዋታቸው ይፋ የሆነው ዛሬ ማለዳ ነው። በአገሪቷ ለውጥ ከመጣ በኋላ ከእስር ከተለቀቁት በሺዎች ከሚቆጠሩ የህግ ታራሚዎች መካከል ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ እድገት እንዲፋጠን የበኩሉን "የማይተካ ሚና ይጫወታል" ተብሎ የክልሉ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ተደርጎ በተሾመው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በተቀነባበረ ሴራ ጥቃቱ መፈጸሙን ነው መግለጫው የሚያመለክተው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፐሬስ ሴክሬተርያት ሃላፊ አቶ ንጉስ ጥላሁን ትናንት ማምሻውን ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ፤ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ከሽፏል። ጥቃት የፈጸሙ ሃይሎችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “የደረሰው በደል በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ሲሉ የገለጹትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የአገሪቷን የሲቪልና የመከላከያ ከፍተኛ አመራር አባላት ሕይወት መቅጠፉ የየክልሎቹ መንግስታትን አሰቆጥቷል፤ ድርጊቱን አውግዘዋል። ይሄው ትናንት በ11:00 ሰዓት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያረጋገጡት። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፉት ሰላሳና አረባ ዓመታት ተሞክሮ የከሸፉና ወደፊትም የማይሳኩ ሀሳቦችን የሚያራምዱ ጥቂት ግለሰቦች የፈጸሙት ተግባር ነው። የአመራር አባለት በጥቃቱ ምክንያት ከመሰዋታቸውና ከመቁሰላቸው በፊት በአገሪቷ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን ብጥብጥ፣ ግድያና ዘረፋ በተመለከተ የጸጥታ ተቋማት ጠንካራ ግምገማ አካሂደዋል። በግምገማውም በየደረጃው ያለው አመራር ስራውን በአግባቡ በማከናወን ህዝቡ ያለ ስጋት ወጥቶ የመግባት ህገ መንግስታዊ መብቱን ለማስከበርና ደህንነቱን ለማስጠበቅ የጸጥታ ሃይሉ ሃላፊነቱን ለመወጣት በመንቀሳቀስ ላይ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸው። አቶ ንጉሱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ጥቃቱ የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን ህዝብ በአጠቃላይ ወደ ብጥብጥ ለማስገባት ታስቦ የተፈጸመ ነው። ጥቃት ካደረሱት መካከል አብዛኞቹ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፌዴራል መንግስት ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው። በዚሁ እለት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ እና በጡረታ የተገለሉት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ ትናንት በኤታማዦሩ ቤት ውስጥ እንዳሉ በገዛ ጠባቂያቸው በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ረፋድ ላይ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ሁለቱ ጄኔራሎች የተገደሉት በተቀነባበረ መንገድ በጠባቂያቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በጡረታ የወጡትን ጀኔራል ሳሞራ የኑስን ተክተው የጦር ሃይሎች የኢታማዦር ሹም የሆኑት ጄኔራል ሰዓረ ደርግን ለመጣል በተካሄደው የትጥቅ  ትግል ጀምሮ ለረጅም ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል። የኤታማዦር ሹም ሃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ሠራዊቱ “ለህዝብና ለአገሩ አንድነት የሚቆም ጠንካራ ሃይል ነው” በማለት የመከላከያ ሰራዊት ለአገሪቷና ህዝቦቿ አንድነት እንዲቆም የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የመከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም ትናንት የተፈጸኘመው አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ጥቃቱ “በግለሰቦች ላይ የተፈጸመ ተራ አደጋ ሳይሆን የኢትዮጵያን የቆየ አንድነት በማደፍረስ፣ በአገር ላይ የመፍረስ አደገጋ መፍጠር፣ መንግስትን ማዳከምና በአጋጣሚውም የግል ዓላማቸውን ለማሳካት የተፈጸመ ተግባር ነው” ብለውታል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊቱ “የተሻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደቱ የበኩሉን ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል” በማለት ነው ሌተናል ጄኔራል ሀሰን የገለጹት። ጄኔራል ሰዓረ እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ ግብአተ መሬት ወታደራዊ ሥርዓት በሚፈቅደው መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል። አገሪቷ በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት ወቅት የዚህ ዓይነት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ የየክልሎች መንግስታትን መሪር ሃዘን ውስጥ የከተተና ያስቆጣ ሲሆን፤ የእርስ በርስ ትብብራቸውን በማጠናከር ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚነሱ ያረጋገጡበት መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ድርጊቱ “ተስፋ በቆረጡ ጥቂት አካላት አማካኝነት በአማራ ህዝብ ላይ ተሰነዘረ ጥቃት በኦሮሞ ህዝብና መንግስት ላይ እንደተፈጸመ ይቆጠራል” ብለዋል። የአገሪቷን ህገ መንግስት በሚጻረር መልኩ የህዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ በመጣል ፍላጎታቸውን ለመጫን የፈለጉ ሃይሎች የፈጸሙት ድርጊት በእጅጉ የሚወገዝና የሚኮነን መሆኑን ነው የክልሎቹ መንግስታት በየመልዕክቶቻቸው አጽንኦት የሰጡት። “የጥፋቱ ዓላማ ከስሯል፤ የተጀመረው የለውጥ ጎዳና በምንም መንገድ እና በማንም ሃይል ሊደናቀፍ አይችልም፤ የሚከፈለው መስዋዕት ሁሉ እየተከፈለ ግቡን እንዲመታ ይደረጋል” በማለት ነው አቶ ሽመልስ የተናገሩት። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የተናበቡና የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ ህዝቡን ለማንበርከክና አገሪቷን ወደ ከፋ አደጋ ለማስገባት የታለመ መሆኑን ነው የገለጹት። በአማራ ክልል የፈጸመውና "ይሳካል" ብለው የጠበቁትን ድርጊት እንዳይከላከል የሰራዊቱን አመራር ለመምታት ታቅዶ የተፈጸመ እኩይ ተግባር ስለመሆኑ ነው ያመለከቱት። በጀኔራል ሰዓረ ላይ የተፈፀመው ግድያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዳይወጣ፣ የአመራር እጦት እንዲከሰትና ኢትዮጵያን ለመበታተን ያነጣጠረ በጽንፈኞች የተሴረ ስለመሆኑ ገልጸዋል። “በአገሪቷ ስልጣን የሚያዘው በውድድር መሆኑን እየታወቀ ለምርጫ ውድድር ድፍረት የሌላቸው ጽንፈኛ ኃይሎች ሰው በመግደል ህዝቡን በጉልበት ለማሰተዳደር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የፈፀሙት ድርጊት ነው” ሲሉ የድርጉቱ ፈጻሚዎችን ምኞት ገልጸዋል። የሱማሌ፣ የጋምቤላ፣ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች፣ የሀረሪ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተሞች አስተዳደሮች በላኩት መግለጫ እንዳረጋገጡት፤ በአገሪቷ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በማይናወጥ መሰረት ላይ ለመገንባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ይህ በሆነበት ወቅት ድርጊቱ በመፈጸሙ በእጅጉ ይወገዛል። በአገሪቷ ዴሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ የለውጥ ስራዎች መካከል ችግሮችና ስኬቶች ቢያጋጥሙም በተለያዩ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን አመላክተዋል። ከጅምሩ ጀምሮ ፍሬ እንዲያፈራ ቀንና ሌሊት እየደከሙ ባሉ የአመራር አባላት ላይ የተፈጸመው ግድያ አውግዘውታል። ህዝቡ በተረጋጋ መንፈስና ሰላሙን ጠብቆ የህዝቡን አንድነት በመጠበቅ ለውጡን እንዲያሳካ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም