ከአገሪቱ ከአንድ ሚሊዮን ያህል ተሸከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ የገቡት ከፊሉ ናቸው

106
ሃዋሳ ሰኔ 15/2011 በአገሪቱ ከተመዘገቡ አንድ ሚሊዮን ያህል ተሸከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ የገቡት ከፊሉ መሆናቸውን የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ኤጀንሲው በተሸከርካሪ አደጋ ሦስተኛ ወገን መድን ሽፋንና በተጎጂዎች አስቸኳይ ህክምና አገልገሎት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ መድረክ በሃዋሳ አካሂዷል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በአገሪቱ ካሉት ተሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ የተገባላቸው 559ሺህ ያህል ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ በአገሪቱ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች የኢንሹራንሱ ተጠቃሚዎች ያልሆኑት ሥራውን ለማስፈጸም በተቋቋሙ አካላት መካከል ቅንጅት ባለመፈጠሩ መሆኑንም አስረድተዋል። ያለሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አደጋ አድርሰው እንደሚጠፉና የጤና ተቋማትም በመንግስት የተፈቀደውን ነጻ ህክምና ስለማይሰጡ ዜጎች ለአካል ጉዳትና ሞት እንደሚጋለጡም ገልጸዋል፡፡ ኤጄንሲው ገጭተው በሚያመልጡና ሽፋን በሌላቸው ተሸከርካሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ የመክፈልና ክትትል የማድረግ ኃላፊነት ሲወጡ እንደማይታይም ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል፡፡ ይሁንና ኤጀንሲው በያዘው የመቶ ቀናት ዕቅዱ ሁሉም ተሸከርካሪዎች ሽፋኑን እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ ኤጀንሲው በዓዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለተጎጂዎች ካሳ የመክፈል ግዴታ ቢኖርበትም ፤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በተገቢው ባለማስገባታቸውንና የካሳ ክፍያው ዝቅተኛ መሆን ክፍያውን ለመፈጸም ችግሮች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በዚህ ዓመት ከደረሱ 15ሺህ በላይ አደጋዎች 3ሺህ የማይሞሉ ብቻ ካሳ እንደተከፈላቸው ተናግረዋል፡፡ የተከፈለውን ካሳ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስመለስ ስልጣን የተሰጠው ኤጀንሲ ከተቋቋመ ጀምሮ ከ300 ለሚበልጡ ተጎጂዎች ካሳ ቢከፍልም፤ እስካሁን ያስመለሰው ገንዘብ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ለተጎጂዎች እስከ 2ሺ ብር የሚደርስ ነጻ አስቸኳይ ሕክምና እንዲያገኙ መንግሥት ቢፈቅድም ፤ ኅብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ  ማጣትና አንዳንድ የጤና ተቋማትም አገልግሎቱን ያለመስጠት ችግሮች እንደሚታዩ ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በተያዘው የመቶ ቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ ዓዋጁ የሶስተኛ ወገን ሽፋንን አስገዳጅ የሚያደርገው ተጎጂዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው ያሉት በኤጀንሲው የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሐሰን መሐመድ ናቸው፡፡ ሶስተኛ ወገን ሽፋን ያላቸው አሽከርካሪዎች የሞት አደጋ ሲያደርሱ ለሟች ቤተሰብ ከ5ሺህ እስከ 40 ሺህ ብር፣ ለአካል ጉዳት እስከ 40ሺህ ብር ካሳ የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የሦስተኛ ወገን መድን ፈንድ ሽፋን ዓዋጁን ለማስፈጸም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት መስራት ያስፈልገዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የክልሎች ን ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚገባም ጠቁዋል፡፡ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህራላህ አብዱላሂ ሚኒስቴሩ ድንገተኛ አደጋዎችን መከላከል ዋነኛው ዓላማው አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በትራፊክ ምክንያት ለሚያጋጥሙ አደጋዎች እስከ 2ሺህ ብር የሚሰጠው ነጻ አስቸኳይ ሕክምናን ጨምሮ ለመድን ፈንድ ኤጀንሲ የሚላኩ የፋይናንስ ሪፖርቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአፍሪካ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኪሮስ ጅራኔ ካሳ ለተጎጂዎች ያልተከፈለበት ምክንያት መገለጽ እንዳለበትና የችግሩን ባለቤት መለየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ዓዋጁ ለአምስት ዓመታት የተገለገልንበት ቢሆንም አሁን ካለው የአገሪቱ እድገት አንጻር ሊሻሻል ይገባዋል ብለዋል፡፡ በመድረኩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ የጤና ተቋማት፣ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተካፍለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም