የመንግስት ውሳኔ ለሁለቱም አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው... የሚዛን ቴፒ ምሁራን

62
ሚዛን ሰኔ 2/2010 የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ለመተግበር ያሳለፈው ውሳኔ ለሁለቱም አገራት ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አለማየሁ አብረሃም እንዳሉት የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው ነው። ተቋርጦ የቆየውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ዳግም ለመመለስና በአገራቱ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ሰሞኑን ያሳለፈው ውሳኔ ለሁለቱም ሀገራት ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ዕሴቶቻቸው የተሳሰሩ ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸው “ውሳኔው በኤርትራ መንግስት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ከሆነ ላለፉት ዓመታት ተለያይተው የቆዩ ወንድማማች ሕዝቦችን ዳግም ለማገናኘት ዕድል ይሰጣል” ብለዋል፡፡ ኢትዮያጵያና ኤርትራ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታታቸው ከማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ባለፈ ለምጣኔ ሀብት ዕድገታቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት መምህር አለማየሁ፣ የአገራቱ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምም ዋጋ እንዳለው አመልክተዋል። እንደመምህሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ መፈረሟ ዓለም አቀፍ ህግን ከማክበሯ ባለፈ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የሚኖራትን ተቀባይነት እያሳደገው ይመጣል። "መንግስት ሁለቱን አገራት ሕዝቦች ሁለንተናዊ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ውሳኔውን ማሳለፉ ተገቢ ነው" ያሉት መምህሩ፣  የሰላም ጥሪው በኤርትራ በኩል ተቀባይነት አግቶ ከተተገበረ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱን አገር ዜጎች ከስጋት ኑሮ ለማላቀቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር መለስ ቸኮል በበኩላቸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በአገራቱና በቀጠናው ሠላም እንዲሰፍን የሚኖረው ፋይዳ የጎላ በመሆኑን ለተግባራዊነቱ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ተሰሚነትና ለቀጠናው ሠላምና ደህንነት ያላትን የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ስለሚያስችልም ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ያልተጠበቀና ድንገተኛ መሆኑን የገለጹት መምህር መለሰ፣ ውሳኔው በሀገራቱ መካከል ሰላምን በማምጣት አገራቱ ዕድገታቸውን እንዲያፋጥኑ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት የመንግስትን ውሳኔ በአልተገባ መልኩ የሚተረጉሙ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ሕብረተሰቡ በእነዚህ ወገኖች እንዳይሳሳት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግስትም በአልጀርሱ ስምምነት ላይ የተቀመጡ አምስት ነጥቦችን ያለ ቅድመ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ለመተግበር መወሰኑ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን እንደሚያሳድገው ጠቁመው፣ በቀጣይ ለአተገባበሩ ጥንቃቄ የተሞላበት እቅጣጫ አስቀምጦ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት በማርገብ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። ከሃያ አመታት ቢፊት በሁለቱ አገሮች መካከል ተፈጠሮ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነትም የብዙ ሰዎችን ሰላም አቃውሷል፤ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም በስጋት ስነ-ልቦና ውስጥ ሆነው እንዲኖሩም ምክንያት ሆኗል። ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ተደርጓል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም