የአማራና የአፋር ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ውይይት እየተካሄደ ነው

59
ሰኔ 14/2011 የአማራና የአፋር ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ ውይይት ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ መካሄድ ጀመረ። በውይይቱ ላይ ከሁለቱም ክልሎች የተወጣጡ የጸጥታ አካላት አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ፀጥታ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገዬ ውይይቱን ሲከፍቱ እንዳሉት የሁለቱም ክልል ህዝቦች የአኗኗርና የባህል እሴቶች አይለያዩም፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ህዝቦች በልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳስረው ፣ ተደጋግፈውና ተቻችለው የአካባቢያቸውን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እንደኃላፊው ገለጻ በሁለቱም ክልሎች በኩል ጥቅመኞች በሚያራምዱት ሴራ አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ይስታዋላሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችንም በጋራ በመፍታት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ታስቦ ፎረሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ  የአካባቢውን ሰላም በማስከበር እስካሁን በተሰሩ ተግባራትንና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለአንድ ቀን በሚካሄደው ውይይት ላይ በምስራቅ አማራና በአፋር ክልሎች ከሚገኙ 8 ዞኖች የተወጣጡ ከ400 በላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም