ጋህአዴን የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

65
ጋምቤላ ሰኔ 14/2011የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋሕአዴን/ የአመራሩን አቅም በማጎልበት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በለውጡ ቀጣይነትና ተግዳሮቶች ላይ የተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ሥልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ለተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትን አቅም የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።፡፡ በተለይም በአመራር ዘንድ ጠንካራ አደረጃጀትና አቅም በመፍጠር በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከአሁን በፊት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ በክልሉ ውጤታማ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩ ጠቁመው “ችግሮችን ለመፍታት የአመራሩን አቅም ማጎልበት ዋነኛ መሳሪያ ነው” ብለዋል። በቀጣይም በከፍተኛ አመራሩ የተጀመረው የአቅም ግንባታ ስልጠና እስከ ታችኛው የመዋቅር እርከን የማዝለቅ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል ፡፡ እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ የተጀመረው ሥልጠና በተለይም ከለውጥ በኋላ ያለውን የአፈጻጸም ሂደት ከማሳየቱም ባለፈ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ለቀጣይ አራት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን የለውጡ ቀጣይነትና ተግዳሮቶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በሚልና በሌሎች ርዕስ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰጥ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም