ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአረንጓዴ ልማት ላይ አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወኑ ነው-የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአረንጓዴ ልማት ላይ አርአያ የሚሆን ስራ እያከናወኑ መሆኑን የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍ ተናገሩ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታዎች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላጅ አባት ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹበትን ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አድርሰዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታም በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገልጸዋል። ሁለቱ አገራት የሚዋሰኑባቸው ኮሪደሮችን በማስተሳሳር ጠንካራ የንግድ ሰንሰለትን ማበጀት በሚመለከት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ሰፊ ምክክር  አድርገናል ነው ያሉት። በጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ መሪነት የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ይበልጥ ይጠናከራል ብለዋል። በኢጋድ ስር በጠቅላይ ሚነኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የሱዳን ተፎካካሪ ሃይሎች ጉዳያቸውን በድርድር እንዲፈቱ የተጀመረውን ጥረት ፍሬ በሚያፈራበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለመትከል ያላቸውን ብርቱ ፍላጎት እንደተረዱ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፤ "እኛም በበረሃማ አገር እንደመኖራችን ይህን አርአያነት ያለው ተግባር መከተል አለብን" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅዳቸው እንደሚሳካ መንገድ እያሳዩ እንደሚገኙ በመጠቆም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም