የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳሉ

74
ሰኔ 13/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ይጫወታሉ። ዱራሜ ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ከምባታ ዱራሜ ከጎንደር ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ19ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ፌደራል ፖሊስ ከድሬዳዋ ከተማ እና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ራሱን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን ቡታጅራ ከተማ በተደጋጋሚ በጨዋታ ሜዳዎች ባለመገኘት ፎርፌ እየተሰጠበት በመሆኑ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ክለቡን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፉም ይታወሳል። በውድድሩ ደንብ መሰረት ፌደራል ፖሊስ እና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች  የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል። በ19ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር የፕሪሚየር ሊጉ መሪ የሆነው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እና መከላከያ ጨዋታ የማያደርጉ አሪፊ ክለቦች ናቸው። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በሊጉ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብ ሲመራ፣ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ28 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ24 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም