ለውጡ ውጤታማ እንዲሆን አሻጋሪ ሀሳቦችን በጥናትና ምርምር ማፍለቅ ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

121
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2011አሁን የተያዘው የለውጥ ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን ውቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበና አሻጋሪ ሀሳቦችን በጥናትና ምርምር ማፍለቅ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ። ''ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትና የለውጥ አመራር'' በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛው የጥናትና ምርምር ጉባኤ  እየተካሄደ ነው። የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ባዘጋጀው በዚሁ ጉባኤ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልል ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት እየተሳተፉ ነው። በአገሪቷ የግጭት መንስኤዎችና መፍትሄዎች፣ከዚህ በፊት የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችና የታጡ ዕድሎች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ለሁለት ቀናት ይመክራል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአካዳሚው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤በኢትዮጵያ ከተጀመረው ለውጥ ጋር የሚስተካከል ማኀበረሰብ ለመፍጠርና የሚገጥሙ ወቅታዊ ችግሮችን በመፍታት ወደተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር አመራሩ ትልቅ ሚና አለው። ''አመራሩ የሚጫወተውን ሚና ለማጉላት ደግሞ አማራጭና አሻጋሪ ሀሳቦች ያስፈልጋሉ'' ያሉት ምክትል  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥናትና ምርምር በመታገዝ አመራሩን የመደገፍ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሕዝቡ የከረረ የለውጥ ፍላጎትና ብርቱ ጥያቄ ውስጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ ከዚህ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መልስ ለመስጠት ብቃት ያለ አመራር ለማፍራት ተከታታይነት ያለው ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። ከዚህ አኳያ አካዳሚው የሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች የሰው ኃይል ልማት ላይ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ቢያሳርፍም አሁንም የበለጠ መስራት ይኖርበታል ሲሉ ተደመጠዋል። በዚህ ምክክር መድረክ የቀረቡ የጥናት ውጤቶች ከተሳታፊዎች ባሻገር ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አካቶ ወደ መሬት የሚወርድበትን ሁኔታ መፍጠር ተገቢ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ለኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት አስፈላጊ ጉዳዮችን ለይቶ ለአስፈጻሚ አካላት በማማከር ረገድ አካዳሚው ተጨባጭ ተግባር ማከናወን ይኖርበታል። የአካዳሚው ፕሬዝዳንት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ በበኩላቸው ትክክለኛ የፖለቲካ አመራር መስጠት ለሠላምና መረጋጋት፣ ኢኮኖሚ እድገትና ማህበረሰባዊ ለውጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። ጠንካራ አገረ-መንግሥትና የሰከነ ብሄረመንግሥት የመሰረቱ አገራት ዘላቂ ልማት እንዳስመዘገቡ የሚጠቅሱት አምባሳደሩ ለዚህ ደግሞ ማሳኪያ ስትራቴጂ ቀይሶ መተግበር ለነገ የማይባል ነው ያላሉ። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ከሁሉ በፊት ሠላም ይቀድማል ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን እርምጃ መወሰድ አለበት የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ መምህር ጋሻው አይፈራም ለውይይት መነሻ የሚሆን ጸሁፍ ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ  በተለያየ ወቅት ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችላት ዕድል ብታገኝም በአግባቡ ሳትጠቀምበት ቀርታለች ባይ ናቸው። አገሪቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኛቸውን ወርቃማ እድሎች አጥታለች ያሉ ሲሆን አሁን የተገኘውን እድል  በአግባቡ ለመጠቀም የፖለቲካ ልሂቃን ተግባብተው መስራት ይጠበቅባቸዋል በማለት ያስገነዝባሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም