ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

69
አዲስ አበባ 13/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጣልያን ምክትል ውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢማኑኤላ ሲ ዴልሪ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። በውይይቱ የጣልያን መንግሥት በልዩ ልዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው የጣልያን ምክትል ውጭ ጉዳይና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢማኑኤላ ሲ ዴልሪ አስታውቀዋል። ኢማኑኤላ ሲ ዴልሪ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ጣሊያን ቅድሚያ ከምትሰጣቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የሁለቱ አገራት የጋራ ሥራዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት ማካሄዳቸውንም አስረድተዋል። ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር በቀጣይነት እንደሚሰሩ ተናግረው ጣሊያን በምትታወቅበት የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ድጋፍ  እንደምታደርግ  አረጋግጠዋል። በዚህም የአክሱም ሐውልትን ለመጎብኘትና የእድሳቱን ዝርዝር ሁኔታዎች ለመመልከት ከመጣው የልዑካን ቡድን ጋር በመሆን አዲስ አበባ መገኘታቸውን ተናግረዋል። በነገው እለትም ወደ አክሱም በማቅናት ሀውልቱ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ እና የደረሰበትን ጉዳት በመመልከት የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚወሰኑ ገልፀዋል። በሌላ በኩል የሁለቱን አገራት የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከር 40 የጣሊያን ተቋማት ትላንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ-ጣሊያን የቢዝነስ ፎረም ላይ መሳተፋቸውንና የጣልያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። ጣሊያን በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች የልማት ዘርፎች ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል። የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትሯ ኢማኑኤላ ሲ ዴልሪ ትላንት ማምሻውን በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ-ጣልያን የቢዝነስ ፎረም ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም