በሀገሪቱ የማዕድን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

71
ሰኔ 12 / 2011 በማዕድን ዘርፍ ያለውን ዕምቅ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ ፡፡ የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ክልል አቀፍ የማዕድን ሀብት ልማት የምክክር መድረክ ትናንት አካሂዷል ፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰፋ ኩምሳ ኢትዮጵያ ለጌጣጌጥ ፣ ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ግብአቶች የሚውሉ በርካታ የማዕድን ሃብት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለው አቅም ልክ ሊመጠቀም ባለመቻሉ ዘርፉ በሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ማበርከት ካለበት አንፃር ሲታይ ብዙም የጎ አስተዋፅዖ አለማበርከቱን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል ፡፡ ባለፉት ዓመታት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ በተለይ ዘርፉ ሊመራበት የሚችል ፖሊሲ ቀርፆ በአግባቡ ማስተዳደር አለመቻል እንዲሁም የአቅም፣ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት ማነስና የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ጠቀሜታ ውስን እንዳደረጉት አብራርተዋል ፡፡ በእዚህም የማዕድን ዘርፍ በውጭ ምንዛሬ ላይ ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ነው የገለጹት ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፀድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ "በዘርፉ ለመሰማራት የሚሹ የውጭ ኩባንያዎችም ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ" ብለዋል ፡፡ የማዕድን ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ ሕገ-ወጥ የማዕድን ዝውውሮችን ማስቀረት፣  ከውጭ የሚገቡና ከማዕድን ጥሬ እቃ የሚሰሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት እንዲሁም በዘርፉ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ማስፋት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ለተግባራዊነቱም መስሪያ ቤታቸው ከክልሎች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡ የማዕድን ዘርፉን በሚገባ በማልማት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል ፡፡ የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ውድና አላቂ የሆነውን ሀብት በተገቢው መንገድ ማልማትና ለህዝብ ጥቅም ማዋል ካልተቻለ ከሰፊው ህዝብ ይልቅ ጥቂቶች ባልተገባ መንገድ የሚበለፅጉበት ፣ ልማት የሚደናቀፍበትና ለግጭት መንስኤ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊከሰት እንደሚችል  አስረድተዋል ፡፡ ዋና ሥራ እኪያጁ እንዳሉት ከዚህ በፊት ከነበረው ዝቅተኛ ትኩረት የተነሳ ሀብቱን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የማስተዳደሩ ተግባር ጉድለት የታየበት ነበር ፤ አልፎ አልፎም የግጭት መንስኤ ሆኖ ቆይቷል ፡፡ የሚወጡ አዋጆችና ደንቦች በአግባቡ ተግባር ላይ አለመዋላቸውን ፣ ህገ-ወጥ አሰራሮችን ለመቆጣጠር የተሰራውም ሥራ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡ ዘርፉን የሚመሩ አካላት ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል ፡፡ "ኤጀንሲው ክልሉ ያለውን የማዕድን አቅም በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል የዘርፉን የውጭ ምንዛሬ ድርሻ ለማሳደግ እያደረገ ከሚገኘው ጥረት ባሻገር ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው" ብለዋል። በ 2011 ዓ.ም ብቻ ከ16 ሺህ በላይ ወጣቶችን በዘርፉ ሥራ ላይ ለማሰማራት መቻሉን አቶ ጥራቱ አብራርዋል ፡፡ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩት የኦርቢት ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ስንታየሁ በሰጡት አስተያየት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሊባል በሚቻል መልኩ በሥራ ዕድልም ሆነ በውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የማዕድናት ክምችት መኖሩን ገልፀዋል ፡፡ እንደ ሀገር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደነበር የገጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት በማዕድን ላይ በስፋት የሚስተዋለው የኮንትሮባንድ ንግድም ተጨማሪ ትኩረት ይሻል ፡፡ ሌላው በማዕድን አቅራቢነት የተሰማሩት አቶ መታሰቢያ ካሳ በበኩላቸው ማዕድናቱ ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልፀው በወጣቶቹ ግንዛቤ ላይ ተጨማሪ ሥራ መስራት እንደሚያስፈል አመልክተዋል ፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የፌዴራል ፣ የክልል ፣ የዞንና  የወረዳ አመራር አካላት እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም