በጭልጋ ወረዳ ወደ ቄያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች የአርሻ ሥራ ጀመሩ

72
ሰኔ 12/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ወደ መኖሪያ ቄያቸው የተመለሱ ከ4 ሺህ በላይ አባወራ አርሶ አደሮች የመኽር እርሻ ሥራ መጀመራቸውን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ገለፁ ፡፡ በወረዳው የእርሻ ሥራ ለጀመሩ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ለግብአትና ለእርሻ በሬ ግዢ የሚውል ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰራጭቷል፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ አቡሃይ ጌትነት ለኢዜአ እንደተናገሩት በወረዳው ተፈናቅለው በመጠለያ የቆዩ ከ16 ሺህ በላይ አባወራ አርሶ አሮችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ ወደመኖሪያ ቄያቸው ከተመሱ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች መካከልም ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት የክረምት የእርሻ ሥራ በመጀመር በቆሎና ገብስ መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ ከ6 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 200 ኩንታል ምርጥ ዘር መቅረቡን ምክትል አስተዳዳሪው ጠቅሰው በመኽር አዝመራው  በተፈናቃዮቹ 10ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የጭልጋ ቀጠና የድጋፍና ክትትል አስተባባሪ አቶ አብርሃም አዛናው በበኩላቸው በግጭቱ ንብረታቸው ለወደመባቸው 1ሺህ 500 አርሶ አደሮች ለእርሻ በሬና ለግብአት መግዣ 18 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡ "ተቋሙ እስከ ሰኔ ማብቂያ ድረስ ተጨማሪ 1ሺህ 500 ለሚሆኑ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ብድር ለማሰራጨት አቅዶ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል፡ ለተፈናቃዮቹ ለእያንዳንዳቸው ከ20 ሺህ  እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ ብድር መሰጠቱንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ "የእርሻ በሬ በመዋስና መንግስት ባቀረበልኝ የበቆሎ ዘር በመታገዝ በሩብ ሄክታር መሬት የዘር ሥራ ጀምሬአለሁ" ያሉት ደግሞ በጭልጋ ወረዳ የአውራርዳ ማርያም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተረፈ ገዳሙ ናቸው፡፡ ከመፈናቀል መልስ በተረጋጋ የኑሮ መንፈስ መደበኛ የእርሻ ሥራ መጀመራቸው እርሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ከእርዳታ እህል ጥበቃ ያላቅቀናል የሚል ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል  ፡፡ በአካባቢው ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው ግጭት የእርሻ በሬ እንደተዘረፈባቸውና ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለወራት እንደቆዩ የገለፁት ደግሞ በወረዳው የላዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይግዛው አረጋ ናቸው፡፡ ወደመኖሪያ ቄያቸው እንደተመለሱም ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር በመውሰድ የእርሻ በሬ ገዝተው የመኽር አዝመራ እርሻ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ወደ ቄያቸው የተመለሱ ተፈናቃይ ወገኖች የግብርና ሙያ ድጋፍና መሰል እገዛ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም