የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሶስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተባለ

52
ሰኔ 11/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መሆኑ ፓሪስ ላይ ተገለጸ። በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሶስተኛ ተከታታይ አመት የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ በመባል ፈረንሳይ ፓሪስ ላይ ተሸለመ። ከዚህ በተጨማሪ አየር መንገዱ በአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ክላስ በሚለው መደብም ተሸላሚ ሆኗል። ህጋዊ እውቅና ያለውና ባለ አራት ኮከብ አለም አቀፍ አየር መንገድ መዛኝ የሆነው ስካይ ትራክስ ፓሪስ ላይ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የታደሙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ሽልማቱን መቀበላቸውን አየር መንገዱ ያደረሰን መረጃ ያሳያል። በዚሁ ወቅት ዋና ስራ አስፈጻሚው "በመንገደኞች በተሰጠ ድምጽ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ምርጥ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ክላስ በመባል በመሸለማችን የላቀ ደስታ ይሰማናል።ዓለም አቀፍ ደንበኞቻችን በእኛ ላይ እምነት በማሳደር ለሰጡን ድምጽ ከልቤ አመሰግናለሁ፤ በተጨማሪ ለተቋሙ ሰራተኞች ያላሰለሰ ጥረትም ያለኝ አክብሮት ከፍ ያለ ነው" ብለዋል። ስካይ ትራክስ በአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ደረጃ አሰጣጥ እጅግ የተከበረ ተቋም ሲሆን የተጓዦችን እርካታ መሰረት በማድረግ ምርጥ ያለውን አየር መንገድ ያሳውቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይትራክስ የሚያዘጋጀውን ሽልማት ቀደም ብሎ መቀዳጀት የቻለ ሲሆን እኤአ በ2018 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ፣ ምርጥ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ክላስ እንዲሁም ሁለት ጊዜ ምርጥ ሰራተኞችን የያዘ በሚለው ዘርፍ ለሽልማት በቅቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ በ2025 ለማሳካት ያቀዳቸውን ግቦች ቀደም ብሎ ማሳካት በመቻሉ አሁን ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ያልተነኩ ገበያዎችን በመዳሰስ ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 115 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ወደ 125 አለም አቀፍ መዳረሻዎች በረራዎችን ያከናውናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም