ህብረተሰቡ ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ ከሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ተጠየቀ

76
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 ህብረተሰቡ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከልና ችግሩ ሲያጋጥምም ጥቆማ እንዲሰጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሳሰበ። በአሁኑ ወቅት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ወረርሽኝ በአፋር ክልል በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ምልክት መታየቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። የበሽታው ምልክት የታየባቸው 447 ህሙማን በዱብቲ፣ አሳይታና ሚሌ ወረዳዎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ህክምና አግኝተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ከክልሉ ጤና ቢሮና አጋር ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ ያደረጉት ቅድመ ዝግጅት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጿል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አጋላጭ ሁኔታዎች በተለይ የክረምት  ወቅት  መግባቱን ተከትሎ በሚፈጠር ዝናብና ጎርፍ ምክንያት በሚከሰት የአካባቢ ንጽህና መጓደል የተለያዩ በሽታዎች መከሰታቸው ይታወሳል። ህብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ ከተበከሉ ውኃ፣ ለምግብነት  የሚውሉና በጥሬያቸው የሚበሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች ንጽኅናቸው በተጓደለ መልኩ ባለማቅረብ፣ ብዙ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው የልማት ኮሪደሮችና ሐይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በሚከበሩባቸው ስፍራዎች፣ የንጽህና መጠቀሚያዎች ላይ ጥንቃቄ በማድረግ እራሱን ከችግሩ መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል። የአተት በሽታዎች ወረርሽኝ በየጊዜው  እንዲከሰት ምክንያት የሚሆኑ የመኖሪያ አካባቢ ጽዳት መጓደል፣ በከተሞች አካባቢ የሚፈጠር የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግር፣ ንጽህናቸው የተጓደሉ  የምግብ  አቅርቦቶች፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና መጓደልና የንጹህ ውኃ አቅርቦት ችግሮች መከላከል እንደሚያስፈልግ ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ለተጨማሪ መረጃና ምክር አገልግሎት በነፃ የስልክ መስመር፡952 ወይም 8335 እንዲደውሉ ሚኒስቴሩ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም