በውላቸው መሰረት ወደ ሥራ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

113
ሰኔ 11/2011 በውላቸው መሰረት ወደ ሥራ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮምቦልቻ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ እሸቱ አሊ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኩ 140 ባለሀብቶች ግንባታ ለማካሄድ 330 ሄክታር መሬት ተረክበዋል። ባለሀብቶች በጨርቃ ጨርቅ፣ በአግሮፕሮሰሲንግ፣ በቆዳ እና ሌጦ፣ በእንጨት፣ በብረታ ብረትና በሌሎች የሥ መስኮች በመሰማራት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ መሬቱ ከሦስተኛ ወገን ነፃ አለመሆኑ፣ በመንግስት የአሰራር ችግር፣ በመሰረተ ልማት መጓደልና በራሳቸው ድክመት አስካሁን በሚፈለገው ልክ ወደ ግንባታና ማምረት ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። መንግስት ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር 153 ሚሊዮን ብር ለመሰረተ ልማትና ለአርሶ አደር ካሳ ወጪ ከማድረግ ባለፈ የአሰራር ክፍተቶችን ፈትሾ በማስተካከል ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በራሳቸው ድክመት በውላቸው መሰረት ወደ ግንባታ ሳይገቡ የተረከቡትን መሬት አጥረው ለሌላ ዓላማ ባዋሉ 19 ባለሀብቶች ላይ አስተዳዳራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። እርምጃ የተወሰደው ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በተደረገው ድጋፍና ክትትል ችግር በታየባቸው ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ እሸቱ፣በእዚህም  ከመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እስከ መሬት መንጠቅ የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል። እስካሁንም ከሁለት ባለሀብቶች ከሦስት ሄክታር መሬት በላይ ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ መግባቱን ነው የገለጹት። እንደ አቶ እሸቱ ገለፃ እርምጃ የተወሰደባቸው ባለሀብቶች ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ መሬት የወሰዱ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ከግማሽ እስከ ስድስት ሄክታር መሬት ይዘው ሳያለሙ በመቆየታቸው ነው። ባለሀብቶች በውላቸው መሰረት ወደ ሥራ እንዲገቡ ያሳሰቡት አቶ እሸቱ፣ “ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ ግንባታ ካልገቡ አሁንም እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሱምያ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ባለሀብቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ ዞኑ የድርሻውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮምቦልቻ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት በፓርኩ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሰኔ13 ቀን 2011 ዓ.ም ከፌዴራል፣ ከክልልና ከደቡብ ወሎ ዞን ከተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላትና ከባለሀብቶች ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዙ ታውቋል 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም