በትራፊክ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

973

ሚዛን ሰኔ 1/2010 በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ትናንት ማምሻውን በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊሲ አስታወቀ፡፡

የጊምቦ ወረዳ ፖሊሲ አዛዥ ኢንስፔክተር መንግስቱ ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ልዩ ቦታው ” ሸንበቶ” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡

አደጋው ሊከሰት የቻለው ከቦንጋ ወደ ጅማ ሲጓዝ የነበረ አነስተኛ የሕዝብ ማመላሻ መኪና በተቃራኒ ከጅማ ወደ ቦንጋ ይጓዝ ከነበረ ሌላ የህዝብ ማመላሻ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአደጋው የአምስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን የገለጹት ኢንስፔክተር መንግስቱ፣ በ25 ሰዎች ላይ ከባድ እንዲሁም በሁለት ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ስድስቱ ወደ ጅማ ሪፈራል ሆስፒታል የተላኩ ሲሆን ቀሪዎቹ በቦንጋ ገብረጻዲቅ ሻዎ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ የአደጋው ምክንያት ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ሲሆን በአደጋውም ሁለቱም ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡