የቴክኒክና ሙያ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ውድድሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

350

ሰኔ 11/2011 የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የፈጠራ፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ውድድሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ከሰኔ 6 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የቴክኒክና ሙያ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የጥናትና ምርምር ውድድርና ሲምፖዚየም ዛሬ ተጠናቋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የክልል ተወካዮች ተገኝተዋል።

አገር አቀፍ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ከጋምቤላ ክልል ውጪ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ ላይ ከ127 በላይ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች የቀረቡ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ከሰልጣኞች ጋር እንዲሁም አሰልጣኞች ከአሰልጣኞች ጋር ሲወዳደሩ ሰንብተዋል።

በሦስት ዘርፎች ማለትም በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት እንዲሁም በጥናትና ምርምር አሸናፊዎች እንደየደረጃቸው ከ9 ሺህ እስከ 23 ሺህ ብር የተሸለሙ ሲሆን የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ከመሬት ውስጥ የውኃ ማውጫ ቴክኖሎጂ፣ የበቆሎ መፈልፈያዎች፣ የእንጨት ሥራ ውጤቶች፣ ፈጠራ የታከለባቸው የአካል ጉዳተኞች የክፍል ውስጥ መቀመጫዎችና የግብርና ተግባራትን የሚያቀላጥፉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ለውድድሩ ከቀረቡት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሐ ግብሩ መዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ትምህርትና ስልጠና የአንድ አገር የዕድገት መሰረት ሲሆኑ በኢትዮጵያም በተለይ ቴክኒክና ሙያ ለአገር ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንዲሆን መንግሥት እየሰራ ነው።

”በአሁኑ ወቅት ትልቅ ደረጃ የደረሱ አገራት አሁን ላሉበት ደረጃ የበቁት የሰው ኃይላቸውን በትምህርትና ስልጠና ስለገነቡ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያለችበት ደረጃ ገና ዳዴ በማለት ላይ በመሆኑ ብዙ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።

 

በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በተለይ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ላይ ክፍተቶች ያሉ በመሆኑ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የክህሎትና የፈጠራ ውድድር መጀመሩ ብቁ ባለሙያዎች እንዲወጡ ከማገዙም ባለፈ በኀብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታትም አዎንታዊ ሚና አለው።

ውድድሩ ያለው አገራዊ ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አሳስበዋ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው ውድድሩ የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ የሚካሄድበት በመሆኑ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

”በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊም ተሸናፊም የለም” ያሉት ፕሮፌሰሯ ዓላማው በዘርፉ ፈጠራን፣ ክህሎትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ በመሆኑ ሁሉም ተወዳዳሪ አሸናፊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የቴክኒክና ሙያ የክህሎት ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውድድር በመስኩ ከፍተኛ መነቃቃት የተፈጠረበት በመሆኑ ለምርት ጥራትና ለተወዳዳሪነት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ እያደገ የመጣውን የአገሪቷን ኢኮኖሚ የሚሸከም ባለሙያ ያስፈልጋል፤ መንግስትም ያለውን ክፍተት ለመሙላት በቴክኒከና ሙያ መስክ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

በአገር አቀፍ ደረጃም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 1 ሺህ 687 መድረሱ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተለይም በመስኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል የአሰራር መሻሻያዎች እየተደረጉ እንደሆነ ያብራሩት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ብሔርች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የመጣው ጌታቸው መሐመድ እስከ 60 ሜትር ድረስ መቆፈር የሚችል የውኃ ጉድጓድ መቆፈሪያ መሳሪያ አቅርቦ ተሸላሚ ሆኗል።

የወርቅ ሜዳሊያና የ23 ሺህ ብር ተሻላሚ የሆነው ወጣቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን የውኃ እጥረት ችግር ለመፍታት እንደዚህ ዓይነት የፈጠራ ውጤቶች ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ወጣት ጌታቸው ተናግሯል።

ብዙ ሰዎች በቀላሉ ውኃ እንዲያገኙ እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ስራዎች ያላቸው ጠቀሜታ ጉልህ በመሆኑም መንግስት ዘርፉን የማበረታት እንቅስቃሴዎችን ሊያጠናክር እንደሚገባም ወጣቱ አመልክቷል።