የካማሽ ዞን ሕዝብ ከ2ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ምርጥ ዘር ከጥፋት በማዳኑ ዕውቅና ተሰጠው

57
አሶሳ ሰኔ 10 / 2011 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሽ ዞን ሕዝብ ከ2ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ምርጥ ዘር ከጥፋት በማዳኑ ዕውቅና ተሰጠው። የዞኑ ሕዝብ ላደረገው አስተዋጽኦ በአሶሳ የምስጋና መርሐ ግብር ትናንት ተካሂዷል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ  በዚሁ ወቅት  እንደተናገሩት የዞኑ ሕዝብ  ባደረገው ጥበቃ በሚኒስቴሩ ስም እውቅና ሰጥተዋል። በያሶና በሎጂጋንፎይ ወረዳዎች የለማው ቢ ኤች ምርጥ የበቆሎ ዘር ምንም ጉዳት ሳይደርስበት 35 ሺህ ኩንታል ዘር መሰብሰቡንም ገልጸዋል። ወቅቱን ጠብቆ ያለመሰብስብ ካልሆነ በቀር ምርቱ ከማሳ ላይ እያለ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት አቶ ሳኒ አመልክተዋል። በግጭቱ ወቅት አምራች ድርጅቶች ፣ ባለሃብቶችና የጉልበት ሠራተኞች ከአካባቢው ወጥተው እንደነበርም አቶ ሳኒ አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ምርጥ  የበቆሎ ዘር ዋና ምንጭ ካማሽ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አምራቾቹ ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሸን ፣ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ምርጥ ዘር አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ናቸው ብለዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች መንግሥታት በአጎራባች አካባቢ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በልማት በማስተሳሰር የፀጥታ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ያደረጉትን አድንቀዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፕራሸን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝና የደቡብ ክልል ምርጥ ዘር አምራች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ አርሶ የካማሽ ሕዝብ በአገር ደረጃ ዝርያውን ከመጥፋት አደጋ መታደጋቸውን ተናግረዋል ። የምርጥ ዘር ማቀናበርያዎችን በዞኑ በመገንባት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ድርጅቶቹ እንደሚሰሩ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በዞኑ በፀጥታ ችግር ደግሞ እንደይከሰት የስጋት ቀጠናዎች ተለይተው ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ምርጥ ዘር አምራች ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና አርሶ አደሩ አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ወደ ምርት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። በዞኑ ባለፉት ወራት በነበረው ግጭት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ፣ 10ሺህዎች ተፈናቅለዋል።ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረትም ወድሟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም