በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ208 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል

79
ነቀምቴ ሰኔ 10 / 2011  በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ208 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት ችግኞቹ የሚተከሉት በ104 ሺህ  በላይ አርሶ አደሮች መሬት ላይ ነው። ችግኞቹ በ73 የመንግሥትና በ5 ሽህ 471 የግል  የቡና  ችግኝ  ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። ሆኖም በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ የዚህ ዓመት ችግኝ ተከላ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ39 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል። በዞኑ  ከ8 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ከ30 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ያረጁ የቡና ዛፎች ተገምድለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ዞኑ ለቡና ልማት ተስማሚነትያለው ከ61 በመቶ በላይ መሬት እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ኤፍሬም፣ አርሶ አደሮች ቡናቸውን በመንከባከብ በምርቱ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ናቸው ብለዋል። በዞኑ የሆማ ወረዳ የአርሰማ ቀበሌ አርሶ አደር ግዛው ደምሴ በሰጡት አስተያየት ወደ ሶስት ሄክታር በሚጠጋ ማሳቸው ላይ ምርጥ ቡና በማልማት ገቢያቸውን ማደጉን ተናግረዋል። በየዓመቱ ከ1 ሺህ 500 እስከ 2 ሺህ ችግኞች በመትከል ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል። በቴክኖሎጂ የተደገፈ በዓመት እስከ 38 ኩንታል ጀንፈል ቡና በማምረት ባገኙት ገቢ በሆማ ከተማ 14 ክፍል ያለው ቤት ሰርተው በማከራየት ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው። የቅልጡ ካራ ወረዳ የጉዮ ሳቺ ቀበሌ አርሶ አደር ፈቀደ ዋቅጅራ በሰጡት አስተያየት በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጣቸው ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው በማምረት በገቢው ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ልጆቻቸውን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ምርጥ የተባሉ ዝርያዎችን በማውጣታቸው በሞዴልነት ተመርጠው መሸለማቸውን ተናግረዋል። ከአራት ሄክታር በላይ የሆነውን ማሳቸውን በምርጥ ዝርያዎች በመሸፈንም በዓመት እስከ 50 ሺህ ብር እያገኙ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በተጨማሪም ወፍጮ ቤት በማቋቋም የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ምዕራብ ወለጋ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በኢትዮጵያ ምርጥ በቡና ምርት ከታወቁ አካባቢዎች አንዱ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም