በባሌ ዞን በትራፊክ አደጋ የ13 ሰዎች ሕይወት አለፈ

123

ጎባ ሰኔ 10/2011 በባሌ ዞን ትናንት ማምሻውን በደረሰው የመኪና አደጋ የ13 ሰዎች ሕይወት ወዲያው ማለፉን የዲሾ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የወረዳው የጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር ዘለቀ በልዩ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው ትናንት ከምሽቱ 12፡00 ላይ የደረሰው በወረዳው ልዩ ስሙ ሆማ ቀበሌ ነው።

አደጋው ከሻሸመኔ ወደ ባሌ ሮቤ ከተማ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲሄድ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ 3 -35653 ኦሮ የሆነው ዶልፊን ሚኒባስ መኪና መንገዱን ለቆ በመውጣት ከሮቤ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ በነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ 3 -85637 ኢት በሆነው ሲኖትራክ  መኪና ስር በመግባቱ ነው።

ኢኒስፔክተር ዘለቀ እንዳሉት በአደጋው በ17 ሰዎች ላይ የሕይወትና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

በትራፊክ አደጋው የ13 ሰዎች ሕይወት ወዲያው ሲያልፍ ሌሎች ከባድ አካል ጉዳት የደረሶባቸው አራት ሰዎች ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኢንስፔክተር ዘለቀ ገለጻ አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ከመንገዱ አቀማመጥ የተነሳ የመኪና ፍጥነትን የሚገድብ ነገር አለመኖሩ በተደጋጋሚ አደጋ እየተከሰተ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።

ለችግሩ በየደረጃው የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መፍትሄ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።