ማዘጋጃ ቤቱ የሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ይሆናሉ

84
አክሱም ሰኔ 7/2011 በትግራይ ክልል የአድዋ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች ጥራታቸው ተጠብቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ። የከተማው ምክር ቤት አባላት ፕሮጀክቶቹን ጎብኝተዋል። የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘርአብሩክ ከጉብኝቱ በኋላ በነበረው ውይይት ላይ እንደተናገሩት  የጥራት ጉድለት የሚታይባቸውን ፕሮጀከቶች አይረከብም። ፕሮጀክቶቹ በተለይ የድንጋይ ንጣፍ(ኮብል ስቶን)ና የተፋሰስ ሥራዎች እየተሰሩ ባሉበት የጥራት ደረጃ   ለመረከብ እንደሚቸገር  አስረድተዋል። የሥራ ተቋራጮች ርክክብ ከማድረጋቸው በፊት ዳግም እንዲያስተካከሉም ፍላጎት እንዳለውም አመልክተዋል። የጥራትና የአፈጻጸም ችግር የሚመለከታቸው ሴክተሮች  በተለይ ማዘጋጃ ቤት፣የኮንስትራክሽንና  ፋይናንስ ጽህፈት ቤቶች ተቀናጅተው ባለመስራታቸው እንደሆነም ተናግረዋል። የከተማው የዓመቱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደካማ እንደነበር ገልጸዋል። የከተማው ምክር ቤቱ አባል አቶ ገብረመስቀል ገብረ ስላሴ በበጀት ዓመቱ በከተማው የተሰሩ ፕሮጀክቶች ጥራት የሌላቸውና ዘላቂ አገልግሎት እንደማይሰጡ አመልክተዋል ። በተለይ የኮብል ስቶንና የተፋሰስ ሥራዎች በቀላሉ ጉዳት የሚደርስባቸውና  የአፈጻጸም ችግር  እንደሚታይባቸው ተናግረዋል። ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ገብረ እግዚአብሔር አስመላሽ በየአካባቢው የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የከተማውን   ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመልሱ ቢሆኑም፤ በጥራትና በጊዜ አፈጻጸም ረገድ ግን ክፍተት አለባቸው ብለዋል። በተለይ በከተማው የተሰራው ረጅም የጎርፍ መውረጃ ቦይ ተገቢውን ጥቅም የማይሰጥና በቀላሉ ሊፈርስ  ስለሚችል ሙሉ ክፍያው ከመፈጸሙና ርክክብ ከመደረጉ በፊት ዳግም ታይቶ የሚስተካከልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አሳስበዋል። ፕሮጀክቶቹ ከዚህ በፊት ከተሰሩ የመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ጥራታቸውን የጠበቁ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ፍትዊ መረሳ ናቸው ። ''ችግሩ በግንባታ ወቅት የሚቆጣጠርና የሚከታተል አካል እንዳልነበረ የሚያሳይ ነው'' ያሉት አቶ ፍትዊ፣  በተለይ ማዘጋጃ ቤቱና የኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ብለዋል። ማዘጋጃ ቤቱ በዚህ ዓመት የሚያስገባቸው 40 ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ከነዚህም  መካከል የአራት ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር ድንጋይ ንጣፍ(ኮብልስቶን) ፣አንድ ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይና ሼዶች  ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም