''የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ''ም/ፕሬዘዳንት ሽመልስ

74
ጎባ ሰኔ 9 / 2011 የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አስገነዘቡ:: በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በክረምት ወራት ሁለት ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት መርሐ ግብር  ትናንት በባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ ዋበሮ ቀበሌ ተጀምሯል። ምክትል ፕሬዘዳንቱ  አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት የክልሉ መንግሥት በአገር ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ከግብ ለማድረስ  ጥረት እያደረገ ነው። በዞኑ የተጀመረውና በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በክረምቱ ወራት የሚቀጥለው መርሐ ግብርም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል። ሕዝቡ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን፤ከገዳ ሥርዓት የወረሰውን ተፈጥሮን የመንከባከብ ባህሉን በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል። በምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተከላው በክረምት ወራት በአገር ደረጃ ለመትከል የታቀደው አራት ቢሊዮን ችግኞች ተከላ መርሐ ግብር አካል መሆኑን ገልጸዋል። መርሐ ግብሩ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ የዞኑን ነዋሪዎች ልምድ ማካፈልና ለጥረታቸውም ዕውቅና መስጠትን ዓላማው ማድረጉን ተናግረዋል። ሕዝቡ ከሚንከባከበው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን የካርቦን ንግድ መርሐ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም  ዶክተር ግርማ አስታውቀዋል። ከኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የወረስነውን ዘመን ተሻጋሪ እሴት ለተተኪው ትወልድ ለማስተላለፍ ለተከሏቸው ችግኞች እንክብካቤ እንደሚያደርጉ የተናገሩት በወረዳው የዋበሮ ቀበሌ ነዋሪ ሼክ አብደላ መንሱር ናቸው። በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉና የዞኑ ካቢኔ አባላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በክረምት ወቅት አራት ቢሊዮን ችግኞች ተከላ መርሐ ግብር ባለፈው ወር መጨረሻ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም