በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተገነባው መንገድ ነገ በይፋ ይመረቃል

91
ሰኔ 8/2011ኢትዮጵያን ከጁቡቲ የሚያገናኘውና የገቢና ውጪ ንግድ እንቅስቃሴውን ያቀላጥፋል የተባለው የድሬዳዋ ደዋሌ 220 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ነገ በይፋ እንደሚመረቅ የመንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። መንገዱ ድሬዳዋን የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆንም ነው የተነገረው። የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የግንባታ ሥራው ላለፉት አራት ዓመታት የተከናወነው የድሬዳዋ ደወሌ 220 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ነገ በይፋ የተመርቆ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል። በኢትዮጵያ መንግስትና ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር የተገነባው መንገድ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ጋር በመንገድ ለማስተሳሰር የተያዘው ዕቅድ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል። አቶ ሳምሶን እንዳሉት ከጁቡቲ ጋር ለሚያስተሳስረው ለእዚህ መንገድ ግንባታ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። "መንገዱ በጁቡቲ በኩል ወደሀግር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ስኬታማ በማድረግ በሀገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብት የልማት ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመዘገብ ያግዛል" ብለዋል። በተለይ በምስራቅ አገሪቱ ክፍል የሚገኙ አርብቶ አደሮች ከእንስሳት ሀብቶቻቸው ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚስችል መሆኑን  ነው የጠቆሙት። እንደአቶ ሳምሶን ገለጻ የድሬዳዋ ደዋሌ መንገድ የፌዴራል፣ የሶማሌ ክልል፣ የድሬዳዋና የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች አመራሮችና ነዋሪዎች በተገኙበት ነገ በይፋ ይመረቃል። “መንገዱ በይፋ ከተመረቀ በኋላ ሁለተኛ የአገሪቱ የክፍያ መንገድ በመሆን ያገለግላል “ ብለዋል አቶ ሳምሶን። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የክፍያ መንገድ የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ሲሆን፣ የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታም ሥራም በመፋጠን ላይ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም