የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚውል የ500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

348

ሰኔ 8/2011 የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚውልና ለአምስት አመት የሚቆይ የ500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካራላይን የድጋፍ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በመልክዓምድር አጠባበቅ መርሃ ግብር ስር ለሚካሄደው የአየር ንብረት ጥበቃ ስራ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ለአምስት ዓመታት የሚቆይ መርሃ ግብር መሆኑ ታውቋል።

ስምምነቱ በተለይ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንክብካቤ ለማድረግና የመሬት መራቆትን ለመከላከል የሚያስችል ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት፤ የአገሪቱ መልክዓ ምድር በተደጋጋሚ ለመሬት መራቆት መጋለጡ የግብርናን ምርታማነት በመጉዳቱ ድህነትን ለመቀነስና ብልፅግናን ለማምጣት አላስቻለም።

መንግስት በዘላቂነት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለማድረግ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ የተቋማት ለውጦችና ተያያዥ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይተል።

የአለም ባንክ መንግስት ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚሰራቸውን ስራዎች እየደገፈ መሆኑን ገልፀው የዛሬው ድጋፍም በተለይ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የመሬት መራቆትን ለመከላከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ለመከወን ይረዳል ብለዋል።

ድጋፉ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር አርሶ አደሮች የመሬት ባለይዞታነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነም ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻልና የደን ሽፋን ለማሳደግ ህብረተሰቡን ለማሳተፍ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት ዘንድሮ እየተካሄደ ከሚገኘው የችግኝ ተከላ ጋር የተገናኘ ነው።

በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካራላይን ተርክ በበኩላቸው ”መርሃግብሩ በደጋማው የሀገሪቱ ክፍል ያሉና የተራቆተ መሬት ያላቸው 5ሺህ ቀበሌዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

ግብርና ለአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት የ45 በመቶ ድርሻ ያለው 70 በመቶ የስራ እድል ፈጠራ 8  በመቶ ለኤክስፖርት ድርሻ ቢኖረውም 50 በመቶ የአገሪቱ ደጋማ ክፍል መሬት የተራቆተ ነው።

ይህ ደግሞ በአገሪቱ የግብርና ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ትልቅ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለውና  በመሬት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣትና  በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

መርሃ ግብሩ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የመልክዓ ምድር ጥበቃ ይደረግለታል እንዲሁም 8 ሚሊዮን አባወራዎች  የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው የሚያስችል እንደሚሆንም ገልጸዋል።

እንዲሁም የአፈር እርጥበታማነት ያሻሽላል የአፈር መሸርሸርን የሚቀንስና ለግብርና መጠቀሚያነት የሚውል ውሃ በበቂ ሁኔታ እንዲኖር የሚያችል እንደሚሆንም አብራርተዋል።

ዳይሬክተሯ የአለም ባንክ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠንና ብልፅግናን ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።