በማዕከላዊ ጎንደር በግጭት ከተቃጠሉት ቤቶች ከ3ሺህ በላያ የሚሆኑት መልሰው ተገነቡ

200

ጎንደር  ሰኔ /2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በነበረው ግጭት በቃጠሎ ከወደሙ መኖሪያ ቤቶች መካከል ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑት ግንባታቸው መጠናቀቁን የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባባሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በዞኑ ጭልጋ ወረዳ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ የተከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ትናንት ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የኮሚሽኑ ከሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ እንደተናገሩት በዞኑ በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም በጭልጋ ወረዳዎች በግጭቱ ወቅት 4ሺህ 361 መኖሪያ ቤቶች በቃጠሎ ወድመዋል፡፡

መንግስት፣ ህዝቡና ረጂ አካላት ባደረጉት የጋራ ርብርብ በአሁኑ ወቅት ከ3ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ከ18ሺህ በላይ ቤታቸው የተቃጠለባቸው አባውራዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ አዲሱ ቤታቸው እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለቤት ግንባታ ሥራው የሚውል ከ150 ሺህ በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር በማቅረብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው የቀሪዎቹ የ1 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጭልጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ ጌትነት በበኩላቸው በወረዳው ተፈጥሮ በነበረ ግጭት 2ሺህ 49 መኖሪያ ቤቶች በቃጠሎ መውደማቸውን አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት በተደረገ ሰፊ እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት ባቀረበው የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር 1ሺህ 567 መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውንና ከ7 ሺህ በላይ አባውራዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ አዲሱ ቤት እንዲገቡ መደረጉን እስረድተዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ በቤቶቹ ግንባታ ሥራ ላይ ሰፊ ተሳትፎ ማበርከቱን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው “በእዚህም 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የባህር ዛፍ እንጨትና 100 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል” ብለዋል፡፡

ከወረዳው በግጭቱ ተፈናቅለው በጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ 16ሺህ የሚጠጉ አባውራዎችና ቤተሰቦቻቸው በአሁኑ ወቅት ወደ ቄያቸው ለመመለስ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው ወደቄያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ህዝቡ የሰላሙ ባለቤትነቱን ተገንዝቦ ሰላሙን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

“ላለፉት አራት ወራት ከነቤተሰቤ በመጠለያ ውስጥ በችግር አሳልፌያለሁ፤ ዛሬ ደግሞ በመንግስትና በህዝቡ ድጋፍ ለአዲስ ቤት በመብቃቴ ደስታዬ ወደር የለውም” ያሉት ደግሞ በጭልጋ ወረዳ የገለድባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት ጫቅሉ ናቸው፡፡

በወረዳው የናራ አውራርዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሳፍንት ሲሳይ በበኩላቸው “መንግስት በሰጠኝ 45 የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር በመታገዝ በገነባሁት አዲስ መኖሪያ ቤት አራት ቤተሰቤን ይዤ አዲስ ሕይወት መኖር ጀምሬአለሁ” ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ማብቂያ በተዘጋጀው ስነ-ስርአት ላይ ተፈናቃዮችን ወደቄያቸው እንዲመለሱና የቤት ግንባታው እንዲሳካ ላደረጉ ግለሰቦች፣ አመራሮችና ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ተገኝተዋል፡፡

ከዞኑአደጋመከላከልምግብዋስትናእናልዩድጋፍየሚሹአካባቢዎችጽህፈትቤትየተገኘውመረጃእንደሚያመለክተውበመጠለያናበዘመድቤትተጠግተውከነበሩ 58ሺህተፈናቀዮችመካከል 43ሺህያህሉወደቄያቸውተመልሰዋል፡፡