በምስራቅ ወለጋ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው

60
ነቀምቴ ሰኔ 1/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን አስር  ወረዳዎች የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች በአርሶ አደሩ የተደረጀ ተሳትፎ የመከላከሉ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞን እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጹ፡፡ ተምቹ በተከሰተባቸው ወረዳዎች በሚገኙ 77 ቀበሌዎች ውስጥ መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የአዝርዕትና ሰብል ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታ አሰበ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም በ1 ሺህ 262 ሄክታር ላይ የሚገኝ የበቆሎ ቡቃያ ማጥቃቱን ያመለከቱት  ቡድን መሪው ተስፋፍቶ  የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ተምቹን በኬሚካል ርጭትና በባህላዊ መንገድ ለማስወገድ እየተደረገ ባለው ጥረት 2 ሺህ የሚጠጉ አባወራ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ለወረዳዎቹ 119 ሊትር ጸረ ተባይ ኬሚካል እየተሰራጨ ሲሆን ተጨማሪ ለማቅረብም ጥረት እየተደረገ ነው። በዞኑ የዲጋ ወረዳ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደምሴ ጊሎ በበኩላቸው በወረዳው ተምቹ ከተከሰተበት 432 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ውስጥ እስካሁን 304 ሄክታሩን ነፃ ማድረግ መቻሉነ ተናግረዋል፡፡ ተምቹን ሙሉ ለሙሉ በመከላከል በወረዳው በበቆሎ የተሸፈነውን ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከተምቹ ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው። በሳሲጋ ወረዳ በ687 ሄክታር የበቆሎ ቡቃያ በተምቹ ጉዳት እያደረሰበት እንደሚገኝ  የገለጹት ደግሞ  የወረዳው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አዱኛ በቀለ ናቸው የተምቹ ስርጭትም አስጊ እየሆነ በመምጣቱ በሙሉ አቅም ለመከላከል እንዲቻል የኬሚካል አቅርቦቱ እንዲፋጠን የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ አዱኛ እንዳሉት አርሶ አደሩም በየቀኑ የእርሻ ማሣውን በመከታተል በባህላዊና በኬሚካል ርጭት ተምቹን ለመቆጣጠር እንዲቻል የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። በግማሽ ሄክታር የበቆሎ ማሳቸው  ላይ የተከሰተውን ተምች ለማስወገድ በኬሚካል እየረጩ  መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪ  አርሶ አደር ፈይሳ ታደሰ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ቤኩማ ብርሃኑ በበኩላቸው በተምቹ የተጠቃውን አንድ  ሄክታር ማሳቸውን ለመታደግ የኬሚካል እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸው መንግስት ኬሚካሉን የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል። የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን በሰጡት አስተያየት ተምቹ በታየባቸው አካባቢዎች በአርሶ አደሩ የተቀናጀ ተሳትፎ 70 በመቶው በባህላዊ መንገድ እና 30 በመቶው ደግሞ በኬሚካል ርጭት መከላከል እንዲቻል መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ የኬሚካል እጥረት እስካሁን እንዳላጋጠመ ጠቅሰው ካስፈለገም  ከኦሮሚያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ጋር በመተባበር የማሰራጨቱ ሥራ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም