በጎንደር ከተማ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የሲሚንቶ አከፋፋይ ድርጅቶችና ልኳንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

140

ሰኔ 7/2011 በጎንደር ከተማ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 33 የሲሚንቶ አከፋፋይ ድርጅቶችና ልኳንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በግብአት ዕቃዎችና በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ መንግስት የተጠና እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

በመምሪያው የውጪ ድህረ ፈቃድ ክትትል ቡድን መሪ አቶ አብልኝ ሙሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሸጋና የማስጠንቀቂያ እርምጃ የተወሰደባቸው 18 የሲሚንቶ አከፋፋይ ድርጅቶችና 15 ልኳንዳ ቤቶች ናቸው፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው የሲሚንቶ አከፋፋይ ድርጅቶች ከፋብሪካዎች በ205 ብር ሒሳብ የገዙትን አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በ500 ብር ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው፡፡

በከተማው የሚገኙ ልኳንዳ ቤቶችም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ ከ60 እስከ 100 ብር የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው በመረጋገጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ጤፍ፣ ሽንኩርትና ድንች በመሳሰሉ የግብርና ምርቶች ላይም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ማስተካከያ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሸቀጦችንና የግብርና ምርቶችን አላግባብ በማከማቸት ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠርም ግብር ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

በከተማው መግቢያና መውጫ በሮች ኬላ በማቋቋም በህገ-ወጥ መንገድ ዝውውር የሚካሄድባቸውን የሸቀጥና የግብርና ምርቶችን ለመቆጣጠር መታቀዱም ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡

“ከሳምንት በፊት በ350 ብር ሒሳብ የገዛሁት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በአሁኑ ወቅት 150 ብር በመጨመሩ የጀመርኩትን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማቋረጥ ተገድጃለሁ” ያሉት የከተማው ነዋሪ አቶ መስፍን አለሙ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ስመኝ ሞላ በበኩላቸው የዛሬ ወር ኩንታሉን በ2ሺህ 500 ብር የገዙት ነጭ ጤፍ በዚህ ወር ወደ 3ሺህ ብር በማሻቀቡ ለመግዛት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

“መንግስት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን በመደገፍና በማጠናከር የዋጋ ማረጋጋት ስራ መድረግ አለበት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ንረት በማስከተል ጤናማ የንግድ ስርአት እንዳይኖር በሚጥሩ ነጋዴዎች ላይ መንግስት በተጠና መንገድ እርምጃ እንዲወስድም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

በከተማው በልኳንዳ ቤት ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ባይለየኝ አበራ በበኩላቸው የከብት ዋጋ በመናሩ ምክንያት የስጋ ዋጋ መጨመሩን ገልጸዋል።